ታህሳስ 28 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:- “መሬትን ለ አራሹ ለምን አላከፋፈልክም ብለን የሀይለሥላሴን ስርዓት እንደማንጠይቅ ሁሉ፤ ዲሞክራሲንም ‘ልማታዊ መንግስት ነኝ’እያለ ከሚቀልደው ኢህአዴግ መጠበቅ የለብንም”ሲሉ ታዋቂው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ተናገሩ።
ዶክተር ዳኛቸው ይህን ያሉት፤ ሰሞኑን በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት(መኢአድ) ጽህፈት ቤት ውስጥ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ነው።
በመኢአድ የውይይት መድረክ ላይ ተጋባዥ ተናጋሪ ሆነው የቀረቡት ዶክተር ዳኛቸው፤ በኢህአዴግ የሚመራው ሥርዓት፤ ዘውዳዊውንና የደርግን አገዛዝ ባህርያት አጥፎ የያዘ ሥርዓት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በፓርቲው ጽ/ቤትውስጥ በተከናወነው በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የዕለቱ ተጋባዥ ተናጋሪ እንዲሆኑ ድርጅቱ ላቀረበላቸው ግብዣ ዶክተር ዳኛቸው ምስጋናቸውን ሲገልጹ፦ “መኢአድ በዚህ መድረክ ላይ ተገኝቼ በተወሰነ ርዕስ ላይ እንድናገር ስለ ጋበዘኝ አመሰግናለሁ፡፡ ኢ/ር ኃይሉን ያየኋቸው ዛሬ ነው፡፡ የኢንጂነርን የፖለቲካ ሳይኮሎጂ አደንቃለሁ” ብለዋል።
አያይዘውም፦ “በዚህ ዝግጅት ላይ የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስጌን ደሳለኝን የጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙን ወላጅ አባት ጠበቃ ዓለሙ ገቤሮን በማግኘቴም ደስ ብሎኛል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ተገኝቼ እንዳስተምር የጋበዙኝን ወ/ሪት መሶቦ ወርቅ ቅጣውንም አመሰግናለሁ” ብለዋል፡፡
“ህጋዊ አስተዳደርና የመብት ጥያቄ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ገለጻቸውን የሰጡት ዶ/ር ዳኛቸው፤ንግግራቸውን የጀመሩት፦ “መባል ያለበት ነገር መባል አለበት ብዬ አምናለሁ” በማለት ነው።
“የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት የነበረውን ባህርይ እናውቃለን፡፡ በመቀጠል አገሪቱን ያስተዳደረው ደርግም፤ የፈፀመውን ፈጽሞ አልፏል፡፡ ኢህአዴግን ሰንገመግመው በአጠቃላይ የሁለቱን ሥርዓቶች ባህርያት አጥፎና አጣምሮ እየሠራ ያለ ሥርዓት ነው” ብለዋል- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ።
“ኢህአዴግ የሚያገባን እኛ ነን፤ እናንተ አፋችሁን ዘግታችሁ ተቀመጡ፡፡ መተቸት ወይንም መቃወም ሳይሆን አድንቁኝ ይለናል”ያሉት ዶክተር ዳኛቸው፤ “ህዝብ የሚያገባው ነገር የለም፡፡ እኛ የምንላችሁን ብቻ ተቀበሉ ማለቱን ተያይዘውታል” ብለዋል፡፡
ዶክተር ዳኛቸው ገለፃቸውን በመቀጠል፦ ፦ “ማንም ሰው በራሱ ላይ ዳኛ መሆን አይችልም፡፡ የአንዱን ንብረት ወስደው ለሌላው የመስጠት መብት የላቸውም፡፡ ኃ/ሥላሴን መሬትን- ለአራሹ ለምን አላከፋፈልክም ማለት እንደማንችል ሁሉ፤ ልማታዊ መንግስት ነኝ ብሎ ከሚቀልደው ከኢህአዴግ መንግስትም- ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መጠበቅ የለብንም”ብለዋል።
ኢህአዴግ የዜጐችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት እየገፈፈ ሁሉንም ነገር ልማታዊ ልማታዊ እያለ መቀለድ ጀምሮአል፤ እስረኞችን ሳይቀር ልማታዊ እስረኛ እያለ እያላገጠ ይገኛል” በማለትም የስብሰባውን ታዳሚዎች ፈገግ አሰኝተዋል-ዶክተር ዳኛቸው፡፡
በቀልድ እያዋዙና ታዳሚውን እያዝናኑ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት ዶ/ር ዳኛቸው፦ “ኢህአዴግ ወስኖና ደምድሞ በመጣ አጀንዳ ላይ የባለ ድርሻ አካላት ውይይት እያለ ውሳኔው እንደማይታጠፍ ሲናገር እንስማለን ፤ለጐጃም- አማርኛ የሚያስተምሩት ይመስል ይህ እስር ቤት ድሮ ደመላሽ ይባል ነበር፡፡ ዛሬ ግን ማረሚያ ቤት ተባለ” እያሉ ያላግጣሉ ብለዋል፡፡
“ኢህአዴግ ራሱን አውራ ፓርቲ ነኝ እያለ ራሱን ይኮፍሳል፡፡ እኛ ጫጩት ነን ማለት ነው” ሲሉ ተሰብሳቢው በሳቅ ያጀባቸው ዶክተር ዳኛቸው፤ “ የኢህአዴግ አገዛዝ የጅብ እርሻ ነው፡፡ ስራው ሁሉ የጥፋት ተግባር ነው”ሲሉ የአገዛዙን የተበላሸ መንገድ ክፉኛ ተችተዋል።
በመሆኑም ምሁራን በስርዓቱ ላይ ጥያቄዎችን ማንሳትና የአገዛዙን የስህተት መንገድ መተቸት እንደሚጠበቅባቸው- ዶክተር ዳኛቸው አሣስበዋል፡፡
“ወጣቱን እፈራዋለሁ” በማለት ማብራሪያቸውን የቀጠሉት ዶ/ር ዳኛቸው፦ “መንግስቱ ኃ/ማርያም በወጣትነቱ ሥልጣን ላይ ወጥቶ ጥፋት አድርሷል፡፡ ለገሠ ዜናዊ በወጣትነቱ ሥልጣን ላይ ወጥቶ በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ነው” በማለት፤ ወጣቱ ኃላፊነት ይረከብ የሚለውን አባባል እንደማይስማሙበት በመጠቆም ንግግራቸውን አጠቃለዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙ በርካታ ታዳሚዎች ላነሷቸው አስተያየቶችና ጥያቄዎችም ዶ/ር ዳኛው መልስ ሰጥተዋል።
በስብሰባው ላይ ተገኝተው የማጠቃለያ ሐሳብ የሰጡት ኢ/ር ኃይሉ ሻወል ፦ “ዶ/ር ዳኛቸው እዚህ ተገኝተህ ስለሰጠኽን ማብራሪያ እናመሰግንሀለን፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን ጓደኞችህን ይዘህ ከድርጅታችን ጐን እንድትሰለፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ ሥልጣን የሚፈልግ እዚህ ቤት አይምጣ፡፡ ለህዝብ እታገላለሁ ለሚል በሩ ክፍት ነው፡፡ እዚህ ሰብስበን ያከማቸነው ሥልጣን የለም፡፡ እዚህ የተሰባሰበው ኃይል ለትግልና ለመስዋዕትነት የተዘጋጀ ነው፡፡ የገጠር ሰው ዛሬም ለእውነትና ለቃሉ ይሞታል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ኢ/ር ኃይሉ አያይዘውም፦ “በዓለም ላይ ዴሞክራሲን በፈቃደኝነት የገነባ መንግስት የለም፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በህዝብ ተሳትፎና ትግል ይገነባል፡፡ ስለዚህ መላው የአገሪቱ ህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ”ብለዋል።