የአማራ ክልል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ቴሌቶን ሊካሄድ ነው

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 6/2011)በአማራ ክልል እና ከክልሉ ወጭ የተፈናቀሉ ከ1 መቶ ሺህ በላይ አማራዎችን ለማቋቋም ታዋቂ ባለሀብቶች የሚሳተፉበት ቴሌቶን በነገው እለት በሼራተን ሆቴል እንደሚካሄድ ተነገረ።

በአማራ ክልል እና ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

ፋይል

በሸራተን አዲስ ሆቴል ነገ በሚካሄደው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ታዋቂ ባለሀብቶችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶኑ 90 ሺህ 736 ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

በአማራ ክልል እና ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም መንግስት  ባለሀብቶችና የአካባቢው ተወላጆች እሰካሁን ያደረጉት ጥረት አነስተኛ ነው በሚል ሲወቀሱ ቆይተዋል።

የአማራ ክልላዊ መንግስት ተፈናቃዮችን ለማቋቋም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ያስፈልገኛል በሚል የእርዳታ ጥሪ ቢያስተላልፍም እስካሁን የተሰበሰበው ከሚፈለገው መጠን ከ6 በመቶ በታች ነው ተብሏል።

ክልላዊ መንግሥቱ ተፈናቃዮቹን ለመርዳት በጊዜያዊነት የሰብዓዊ ዕርዳታዎችን እያደረገ መሆኑን ይገልጻል።

ይሕም ሆኖ ግን ተፈናቃዮችን  በዘላቂነት  መልሶ ለማቋቋም የአቅም ችግር እንዳለበት ነው የሚገለጸው፡፡

እናም የሚፈለገውን የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የገንዘብ መጠን እና የቁሳቁስ ድጋፍ ለመሰብሰብ ነገ መጋቢት 7/ 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል ቴሌቶን ለማዘጋጀት መርሀ-ግብር ተይዟል፡፡

የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶኑ 90 ሺህ 736 ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

ከቤታቸው ተፈናቅለው ለሚገኙ አርሶ አደሮች የክረምት ጊዜ ከመድረሱ በፊት ለእርሻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላትም ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

በቴለቶን ዝግጅቱ ዕርዳታ ከመሰብሰብ ባሻገር የአማራና የኦሮሞ አንድነትና  የአብሮነት መልዕክቶች በመድረኩ እንደሚተላለፉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በቴለቶኑ ታዋቂውን ባለሀብት አቶ በላይነህ ክንዴን ጨምሮ በርካታ የአማራ ባለሀብቶችና የኦሮሚያ ክልል ባለሀብቶች አጋርነታቸውን በማሳየት ሕዝቡ ‹‹የኦሮሞ ደም የኔ ደም ነው። የአማራ ደም የኔ ደም ነው›› በመባባል ከዚህ በፊት ያሳየውን አጋርነት በተግባር ያስመሰክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ለእርዳታ ማሰባሰቡ ከባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከዲያስፖራዎች እና ሌሎች አካላት ዕርዳታ ለማግኘት ንዑስ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ተግባር መገባታቸው ነው የተጠቆመው፡፡

ተልዕኮውን ‹‹አግዛለሁ›› የሚል እና ዕርዳታ ለማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ቅን ዜጋ በተለያዩ ባንኮች በተከፈቱ የሒሳብ ቁጥሮች ማስገባት እንዲችልም ቁጥሮቹ ይፋ ተደርገዋል፡፡