(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 3/2011)የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ዑስማን ከኃላፊነታቸው ለቀቁ።
አቶ ኢብራሂም ዑስማን ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ለከተማ አስተዳደሩ ያቀረቡት ጥያቄ በምክር ቤቱ ተቀባይነት አገኝቷል፡፡
በምትካቸውም ምክርቤቱ አቶ መሐዲ ዲሬን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ በማድረግ ሹሟል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በነበሩት አቶ ኢብራሂም ዑስማን ላይ በተደጋጋሚ በሚደረጉ ሠልፎች ተቃውሞ ይቀርብባቸው ነበር፡፡
ድሬድዋ ከተማዋን በፈረቃ በሚያስተዳድሩ ፓርቲዎች ስትታመስ መቆይቷም ነው የሚታወቀው።
አንዴ ሶህዴፓ ሊላ ጊዜ ደግሞ በኦዴፓ ካድሬዎች በፈረቃ የምትተዳደረው ድሬድዋ 40፥40፥20 በሚባለው የኮታ አስተዳደር የምትመራ በመሆኗ ሊሎች ብሄረሰቦች ከፍተኛ በደል ይደርስባቸው ነበር።
በዚሁ ምክንያት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት አቶ ኢብራሂም ዑስማን ስልጣን እንዲለቁ በሕዝቡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቆይተዋል።
አሁን ግን አቶ ኢብራሂም ዑስማን በመጨረሻም ቢሆን የከንቲባነት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) አባል የሆኑት አቶ ኢብራሂም ለሦስት ዓመታት ከመንፈቅ በከንቲባነት አገልግለዋል።
ስልጣን የመልቀቅ ጥያቄያቸውን የተቀበለው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በምትካቸው አቶ መሐዲ ዲሬን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ በማድረግ ሹሟል፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 2ኛ የስራ ዘመን 5ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በዛሬው እለት ስብሰባወን በማካሄድ የተለያዩ ሹመቶችን አፅድቋል።
በዚሁም መሰረት አቶ አብደላ አህመድ፦ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ፥አቶ ከድር ጁሀር፦ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ፥አቶ አብዱሰላም አህመድ፦ የግብርና፣ ማእድን እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ፥ወይዘሮ ሙሉካ መሀመድ፦ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፥አቶ ሙሳ ጠሀ፦ የፍትህ ፀጥታ እና ህግ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፥ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ፦ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አድርጎ መሾሙን ዘገባዎች አመልክተዋል።