(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 26/2011) በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 105 ክላሽንኮቭ የጦር መሳሪያ መያዙን የቡራዩ ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።
ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ ትናንት ሌሊት መያዛቸውን ለማወቅ ተችሏል ።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም ከጋምቤላ ክልል ወደ አማራ ክልል በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ በፀጥታ አካላት ጥምረት በቑጥጥር ስር ውሏል።
105 ክላሽንኮቭ የጦር መሳሪያዎቹ የተያዙት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት ነው።
የቡራዩ ከተማ ፖሊስ፣ ልዩ ሀይል እና የብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት በጥምረት ባከናወኑት ስራ ትናንት ከሌሊቱ 6 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት በነበረው ጊዜ የጦር መሳሪያዎቹ ተይዘዋል።
በወቅቱ በቡራዩ ከተማ አሸዋ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተደረገ ፍተሻ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል ሲደረግ እንደነበርም ነው የተነገረው።
እናም ከአሸዋ ሜዳ ተሽከርካሪውን በማሸሽ ለማምለጥ ሲሞክሩ በተደረገ ክትትል አምቦ ከተማ ሲደርሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የቡራዩ ፖሊስ አስታውቋል።
በዚሁ መሰረት ለውዝ ጭኖ በነበረ አይሱዙ ኤፍ.ኤስ.አር የጭነት ተሽከርካሪ ላይ 42 ታጣፊና 63 ባለሰደፍ በድምሩ 105 ክላሽንኮቮች፣ 95 የክላሽንኮቭ መጋዝኖች እና 5 ጥይት ተይዟል ተብሏል።
ከአይሱዙ ኤፍ.ኤስ.አር የጭነት ተሽከርካሪው ፊት በመሄድ ሁኔታዎችን ሲያመቻች የነበረ አንድ ዶልፊን አሽከርካሪም በቁጥጥር ስር መዋሉን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም ከጋምቤላ ክልል ወደ አማራ ክልል በርካታ የጦር መሳሪያዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ በፀጥታ አካላት ጥምረት በቁጥጥር ስር ውሏል።
በዚህ ተሽከርካሪ ወስጥ ምን ያህል የጦር መሳሪያ እንደተያዘ ግን የተገለጸ ነገር የለም።