የመለስ አገዛዝ በዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለው ዘግናኝ ድርጊት ተባብሶ ቀጥሏል

ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ክልል አንዲት የመኢአድ አባል በ 28 ጥይት ተደብድባ ስትገደል፤ በሰሜን ጎንደር በበለሳ ወረዳ  አንድ የመኢአድ ስራ አስፈፃሚ- አናቱን በመጥረቢያ  ተመትቶአል።

የአንድነት ልሳን የሆነው ፍኖተ-ነፃነት እንደዘገበው፤በደቡብ  ክልላዊ በደራሼ ልዩ ወረዳ በሠገን የምርጫ ክልል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን /መኢአድን/ በመወከል በምርጫ 2002 ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተወዳደረችው ወ/ሮ አማረች ገለኔ በአገዛዙ ታጣቂዎች በ28 ጥይት ተደብድባ  በሚያሰቅቅ ሁኔታ ተገድላለች።

ከዚህም በላይ የ10 ዓመት ልጇ ፀዳለች ገልገሌ በጥይት ጀርባዋ ላይ ፤ የሁለት ዓመት ልጇ ፈይሳ ገልገሌም እንዲሁ በጥይት  ጉልበቱ ላይ  መመታቱን የገለጹት የመ ኢአድ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ወይዘሮ መሶበ ቅጣው፤ ልጆቹ ግን በህይወት መትረፋቸውን ተናግረዋል።

በሰሜን ጐንደር ዞን የበለስ ወረዳ የመኢአድ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው አቶ ብርሃኑ አቡሐይ ደግሞ በአገዛዙ ሀይሎች  ጭንቅላቱን፣ ወገቡንና ክንዱን  በመጥረቢያ መመታቱን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ወ/ሪት መሶበ  ገልጸዋል።

“ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች፣ ደህንነቶችና ታጣቂዎች ከህግ በላይ በመሆን በአባሎቻችን ላይ እጅግ ዘግናኝ የሆነና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እየፈፀሙ  ነው”ያሉት ወይዘሮ መሶበ፤ “እነዚህን ህገ-ወጦች በየትኛውም የህግ አካል ማስታገስ አልተቻለም”ሲሉ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

 

“ ወይዘሮ አማረችን  በ28 ጥይት  ደብድበው ከገድሉና ሁለት ልጆቿን ካቆሰሉ በሁዋላ እነሆ የፈፀሙት አልበቃ ብሏቸው ባለቤቷን አቶ ገልገሎ ኮኘታን በየዕለቱ ዛቻና ማስፈራሪያ እየፈፀመበት ይገኛሉ” ብለዋል-ወይዘሮ መሶበ።

በሌላ በኩል  በሰሜን ጐንደር የበለሳ ወረዳ መኢአድ ሥራ አስፈጻሚ  የሆኑትን አቶ ብርሀኑ አቦሀይን ፦” ለምን የመኢአድ አባል ሆንክ? ለምንስ ትቃወመናለህ?” በማለት ሁለት የአካባቢው የኢህአዴግ ሀላፊዎች ልክ እንደ እንጨት ፈልጠውታል ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሀላፊዋ፤ የሰዎቹ ማንነት በግልጽ የሚታወቅ ቢሆንም፤ ገለልተኛ  የፍትህ አካል ማግኘት ባለመቻሉ  ለህግ ማቅረብ አልተቻለም ብለዋል፡፡

“ይህም  ሥርዓቱ በግልጽ ወደ  ተራ ወንጀል ውስጥ መግባቱን ያሳያል” ሲሉም ወይዘሮ መሶበ  አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል በደቡብ ክልል ውስጥ፦-“ የኢህአዴግ ባለሥልጣናትን የግል ሥራ አንሰራም” በማለታቸውና በአካባቢው ያሉትን የመኢአድ አባላት ስም ዝርዝር እንዲያቀርቡ ተጠይቀው እንቢ በማለታቸው ሰሞኑን ለእስር ተዳርገው የነበሩት 27 የመኢአድ አባላት በዋስ መፈታታቸውን ከደቡብ ክልል መኢአድ ጽ/ቤት የደረሳቸውን መረጃ በመጥቀስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

መኢአድ በምርጫ 2002 ከኢህአዴግ ጋር የስነምግባር ደንብ መፈራረሙ ይታወሳል።

ምንም እንኳ በወቅቱ አቶ መለስ ዜናዊ በመኢአድ አባላት ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ወከባ ድርጅታቸው አጣርቶ እርምጃ እንደሚወስድ ለ ድርጅቱ ሊቀመንበር ኢንጂነር ሀይሉ ቃል ቢገቡላቸውም፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመኢአድ አባላት ላይ የሚደርሰው እንግልትና ወከባ አልቀነሰም።

ገዢው ፓርቲ በቅርቡ በመድረክ አባላት ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መፈጸሙን መዘገባችን ይታወሳል።