(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 6/2011)የሕወሓቱ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በአማካሪነት መመደባቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ።
አቶ አስመላሽ ከኢሕአዴግና ከሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው በተጨማሪ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል።
በቅርቡ ተካሂዶ ከነበረው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ በኋላ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በአማካሪነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል።
አቶ አስመላሽ ላለፉት በርካታ ዓመታት በፓርላማ በመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትርነት ሲሠሩ የነበረ ቢሆንም፣ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ በስራ ላይ አልነበሩም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለፓርላማው በላከው ደብዳቤ፣ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ሆነው ሲሠሩ የነበሩትን አቶ አስመላሽ ከኃላፊነት አንስቷል።
በአቶ አስመላሽ ምትክም ቀደም ሲል በፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሆነው የተሾሙት የኦዴፓ አባል አቶ ጫላ ለሚ ኋላፊነቱን ለጊዜው እንዲረከቡ ተደርጓል።
ከወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ነባር የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሮችን መልሰው እንዳይሾሙባቸው የፓርላማ አባላት ጠይቀው እንደነበርም ታውቋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ተነስቶላቸው ለነበረው ጥያቄም መንግሥት የመንግሥትን ጥቅም ሊያስከብሩ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን እንደሚመድብ ገልጸው ነበር።
በአሁኑ ጊዜ በፓርላማው የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ድኤታ ሆነው ሲሠሩ የነበሩ አራት ሰዎች ተነስተው በምትካቸው ሌሎች ተሹመዋል።
ኦዴፓን በመወከል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ጌታቸው በዳኔ ተነስተው በአቶ ጫላ ለሚ ተተክተዋል።
ደኢሕዴንን በመወከል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩት አቶ አማኑኤል አብርሃም ምትክ ደግሞ አቶ መስፍን ቸርነት ተመድበዋል።
ሕወሓትን በመወከል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ድኤታ በነበሩት አቶ አፅብሃ አረጋዊ ምትክ ደግሞ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ ቦታውን ይዘዋል።
አዴፓን በመወከል የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ድኤታ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሲያገለግሉ በነበሩት አቶ መለስ ጥላሁን ምትክ ደግሞ አቶ ጫኔ ሽመካ መተካታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ላለፉት በርከት ያሉ ወራት ሕወሃትን የሚወክል ሰው በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ውስጥ አለመኖሩን የጠቆሙት ምንጮች፣ የአቶ አስመላሽ በኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት መመደብ ይኼንን ክፍተት እንደሚሞላ ጠቁመዋል።