(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 6/2011)ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወደ ውጭ በሕገወጥ መንገድ እንደሸሸባት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አስታወቀ።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የአፍሪካ የጤና ክብካቤና የኢኮኖሚ ዕድገት ሪፖርት እንዳመለከተው ይህ ገንዘብ ኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ የምታውለውን 87 በመቶ በጀት ይሸፍናል።
በአዲስ አበባ ይፋ የተደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ኣኝደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2012 ባሉት ዘጠኝ ዓመታት በየዓመቱ ከ2.2 ቢሊየን ዶላር በላይ በሕገወጥ ገንዘብ በሚያሸሹ አካላት ሳቢያ ተጎጂ ሆናለች ብሏል፡፡
በዚህ ሳቢያም ለጤናው ዘርፍ የምትመድበው ዝቅተኛ በጀትም በሚሸሸው ገንዘብ ምክንያት ከባድ ተፅዕኖ ውስጥ እንደቆየ ነው የገለጸው፡፡
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ኢኮኖሚዋ (ከአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት አኳያ) አንድ በመቶ ለጤናው ዘርፍ ትመድባለች።
በአንፃሩ በየዓመቱ ከ2.2 ቢሊየን ዶላር በላይ እየሸሸባት በመሆኑ 87 በመቶው የጤናውን ዘርፍ በጀት ወደ ውጭ የሚሸሸው ገንዘብ እንደሚሸፍነው ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በዚሁም ሳቢያ መንግሥት ለጤናው ዘርፍ ከሚያወጣው ወጪና ለዕዳ ክፍያ ከሚያውለው ገንዘብ ተቀናንሶ ሲሰላም፣ አገሪቱ በየዓመቱ የ2.5 ቢሊየን ዶላር የበጀት ክፍተት ይገጥማታል ተብሏል፡፡
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2015 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ብቻ የኢትዮጵያ መንግሥት አማካይ ጠቅላላ የዕዳ ክምችት መጠን 55 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ የተባበሩት መንግስታት ማስታወቁን ሪፖርተር ዘግቧል።
ለዕዳ ክፍያ የሚውለው ከፍተኛ ገንዘብ እንደ ጤናው መስክ ሁሉ ባሉት መሠረታዊ ዘርፎች ላይ ጫና ማሳደሩንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሪፖርት አመልክቷል፡፡