(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2011)በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 46ሺህ መድረሱ ተገለጸ።
በህወሃት አገዛዝ ቀጥተኛ የመሳሪያና የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ ነው በተባለው በዚሁ ግጭት በ12 ቀበሌዎች የሚገኙ ቤቶች በእሳት መውደማቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ከቅማንትና ከአማራው ማህብረሰብ የተፈናቀሉት እነዚህ ዜጎች በምግብና ውሃ እጥረት ስቃይ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።
ተፈናቃዮቹ በአርማጮሆና ደምቢያ አካባቢዎች ተጠልለው ይገኛሉ።
አስቸኳይ እርዳታ እንዲቀርብላቸው የጠየቁት ተፈናቃዮች አለበለዚያ በበሽታና በረሃብ የሚደርሰው ሰብዓዊ ጥፋት ከፍተኛ ይሆናል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ሳምንታት ይበልጥ ግጭቱ መባባሱ ለተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል።
በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተፈጠረው ግጭት ሁለቱንም ወገኖች ተጎጂ ማድረጉን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ባለፈው ሳምንት የተጀመረውን ዛሬም ድረስ አልፎ አልፎ የቀጠለው ግጭት ካደረሰው የሰው ልጅ ሞትና የአካል ጉዳት በተጨማሪ ለበርካቶች መፈናቀል ምክንያት መሆኑም ታውቋል።
በሁለቱ ዞኖች ውስጥ 46 ሺህ ዜጎች በግጭቱ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እንደሚገኙ የአማራ ክልል ባለስልጣናት ይገልጻሉ።
ከጭልጋ፣ ደምቢያና ላይ አርማጭህ አካባቢዎች የተፈናቀሉት እነዚህ ዜጎች በትክል ድንጋይ አቅራቢያና በደምቢያ አይምባ ቀበሌዎች እንደተጠለሉም የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።
ከሁለቱም ወገኖች የተፈናቀሉት ዜጎች የሚበላና የሚጠጣ ነገር ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን የገለጹ ሲሆን አስቸኳይ እርዳታ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።
አሁን ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ የሚገልጹት ተፈናቃዮች በተፋፈገ ሁኔታ በአንድ አካባቢ ታጭቀው መኖራቸው ለተለያዩ በሽታዎች እንዳጋለጣቸውም ገልጸዋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች መንግስት በቂ ምግብ እና ቁሳቁስ እንዲያቀርብላቸው መጠየቃቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሁለቱ የጎንደር ዞኖች የቅማንት ጥያቄ መነሻ ሆኖ የተቀሰቀሰው ግጭት የሌሎች ወገኖች እጅ እንዳለበት ይነገራል።
የአማራ ክልል የሰላምና የደህንነት ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ለኢሳት እንደገለጹት የህወሃት ቡድን የቅማንት ኮሚቴ ነን በሚል ላደራጃቸው ሃይሎች በሚሰጣቸው የገንዘብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ አካባቢውን የቀውስ ቀጠና አድርጎታል።
በተመሳሳይ የአማራ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሰማህኝ አስረስ በስም ባይጠቅሱም ሶስተኛ ወገን እጁን አስገብቶ በከባድ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ክልሉ ላይ አደጋ ጥሏል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አዴፓ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ከደህንነትና ጸጥታ አመራሮች ጋር በባህርዳር ዝግ ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የስብሰባው ውጤት አልተገለጸም።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት አዴፓ በዝግ በሚያደርገው ስብሰባ የማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተከሰተውን ግጭት እንደሚነጋግርበትና ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
ጣልቃ በመግባት የክልሉን ሰላም እያደፈረሰ ያለውን የህወሃትን ቡድን በይፋ ሊያወግዝ እንደሚችልም ከኢሳት ምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።