ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-በደቡብ ኢትዮጵያ የተፈጠረው የጎሳ ግጭት ድንበር ተሻግሮ ኬንያ ውስጥ የሚገኙ ጎሳዎችንም እያተራመሰ ነው ተባለ
በደቡብ ኢትዮጵያ በቦረናና በገርባ ጎሳዎች መካከል ከግጦሽ መሬትና ከውሀ ጋር በተያያዘ በተነሳው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል።
ግጭቱ ወደ ኬንያም ተስፋፋቶ በአካባቢው የሚገኙ 17 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ታወቋል።
ከአካባቢው ርቀት አንጻር እስካሁን ድረስ የተጠናከረ መረጃ ባይቀርብም፣ በሞያሌ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደሚሉት በግጭቱ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ብዙዎችም አካባቢውን እየለቀቁ ተሰደዋል።
በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ ደግሞ በሶማሊ እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል በቅርቡ የተፈጠረው ግጭት ፣ ዳግም ያገረሻል የሚል ፍርሀት መኖሩን የአካባቢው ነወራዎች ገልጠዋል።
ሞያሌን የሶማሊ እና የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ከሁለት ከፍለው የሚያስተዳድሩዋት ሲሆን፣ በሁለቱ ብሄሮች ግጭት የከተማው ሰላም በተደጋጋሚ ሲደፈርስ ቆይቷል።
በቅርቡ ከትምህርት ቤት ንብረት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶች አሁንም አካባቢውን እንደተቆጣጠሩት ነው።