(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2011)ሴራሊዮን በሐገሯ በሴቶች ላይ የሚፈጽመው አስገድዶ መድፈር አሳሳቢ ሆኖ በመገኘቱ የድንገተኛ ጊዜ መመሪያ ማውጣቷን አስታወቀች።
ሴት በመድፈር የተጠረጠረና የተፈረደበት ሰው በእድሜ ልክ እስራት እንደሚቀጣም የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት አስታውቀዋል።
በሴራሊዮን በሴቶች ላይ የሚፈጸመው አስገድዶ የመድፈር ወንጀል እየጨመረና አሳሳቢ ሆኖ መገኘቱን በመግለጽ የድንገተኛ ጊዜ መመሪያ መውጣቱን ትላንት በርዕሰ መዲናዋ ፍሪታውን ያስታወቁት የሐገሪቱ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳባዩ መንግስት አደጋውን ለመቀነስ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም ሴቶችን በተለይም ሕጻናትን የደፈሩ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቃቸዋል ብለዋል።
7 ነጥብ 5 ሚሊየን ያህል ሕዝብ የሚኖርባት ሴራሊዮን ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ብቻ 8 ሺህ 500 ወሲባዊ ጥቃትና አስገድዶ መድፈር ተመዝግቦባታል።
ይህም ከቀድሞው አመት ጋር ሲነጻጸር በ4 ሺ መጨመሩንም ከቢቢሲ ዘገባ መረዳት ተችሏል።