(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2011)የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ ተሻሽሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ ተገለጸ፡፡
ማሻሻያው የሥራ አመራር ቦርዱ አባላትን ከ9 ወደ 5 ዝቅ እንዲል አድርጓል፡፡
ቦርዱ ለ3 የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሕጋዊ እውቅና መስጠቱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች በትርፍ ጊዜያቸው ሳይሆን በቋሚነት ሙሉ ጊዜ እንደሚሰሩ እና በ5 ዓመታት ብቻ ተገድቦ የነበረው የሥራ ዘመናቸውም እንዲራዘም መደረጉን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለአራት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህጋዊ እውቅና መስጠቱን የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለ2 አገር አቀፍና ለ2 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ ለ4 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕውቅና ሰጥቷል።
የምርጫ ቦርዱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ እና ምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ /ምክክር/ ከአገር ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች እውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡
እውቅና የተሰጣቸው የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ቅዴፓ/ እና የጋምቤላ ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ /ጋህነን/ ናቸው።
ቦርዱ ለፓርቲዎቹ ዕውቅና የሰጣቸው በሕጉ መሰረት የተቀመጡትን መስፈርቶች አሟልተው በማቅረባቸው መሆኑን አስታውቋል።