(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2011)በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ሹመት ተሰጣቸው።
ከንቲባው አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በሐዋሳ ከተማና አከባቢዋ በአንዳንድ የሲዳማና የወላይታ ብሔረሰብ አባላት መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ እጃቸው አለበት በሚል ከሌሎች የከተማው አመራሮች ጋር ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወቃል።
አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ክስ እንደቀረበባቸው ቢታወቅም ለክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በምክትል ሃላፊነት ደረጃ የአስተዳደርና ፋይናንስ ሃላፊ ሆነው እንዲሰሩ የደቡብ ክልል መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ሹመት እንደሰጣቸው ነው የተሰማው።
በፌደራል ጠቃላይ አቃቤ ህግ ክስ የተመሰረባቸው የሀዋሳ የቀድሞ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ ይባላሉ።
ከአንድ ወር በፊት በፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በይፋ እንደተገለጸው አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በሀዋሳ ከተማና አከባቢዎ በአንዳንድ የሲዳማና የወላይታ ብሄረሰብ አባላት መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ እጃቸው አለበት ተበለው ከሌሎች 33 ሰዎች ጋር የክስ ፋይ ተከፍቶባቸዋል።
የአቃቤ ህግ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የተፈጸመውና በርካታ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት የከንቲባው እጅ እንዳለበት በተለያዩ ማስረጃዎች ተረጋግጧል።
እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በነበራቸው ሚና ችግሩን ከመቆስቆስ በተጨማሪ እንዲባባስ አድርጎታል ይላል የአቃቤ ህግ ፣ማስረጃ። ለጠፋው ህይወትና ለደረሰው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከንቲባው ቴዎድሮስ ገቢባና ሌሎች አመራሮች ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸውም ያትታል።
በዚያም መስረት ነው ከንቲባውና ሌሎች አመራሮች ላይ ክስ የተመሰረተው።
ከስድስት ወራት በኋላ፡ የአቃቤ ህግ ክስ በሂደት ላይ እያለ ግን በከባድ ወንጀል የሚጠየቁት የሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በክልሉ መንግስት ሹመት እንደተሰጣቸው ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ ላይ የተመለከተው።
በቁጥር 2 – 1- 29 1123/5074 በቀን 26 አምስተኛ ወር 2011 ከደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ለክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት የተጻፈ ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው፡ በፌደራል አቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸው በሂደት ላይ ያሉት አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ በምክትል ሃላፊነት ደረጃ የቢሮው የአስተዳደርና ፋይናንስ ዘረፍ ሃላፊ ተደርገው መሾማቸውን ይገልጻል።
ለተለያዩ የክልሉ ቢሮዎች ግልባጭ በተደረገው በዚሁ ደብዳቤ ላይ አቶ ቴዎድሮስ ከጥር 22 ጀምሮ በተመደቡበት ሃላፊነት ስራቸውን በመጀመር በትጋትና በታማኝነት እንዲወጡት ማሳሰቢያ ተካቶበታል።
በአጠቃላይ አቃቤ ህግ በከባድ ወንጀል ክስ የሚፈለግ ግለሰብ ሹመት መሰጠቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ደቡብ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ደውለን ምክትል የቢሮ ሃላፊውን አነጋግረን ስለጉዳዩ ቢያውቁም ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ ገልጸውልናል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው ግለሰብ በደቡብ ክልል መስተዳድር ሹመት የተሰጠቸውን የሀዋሳ ከተማ የቀድሞ ከንቲባን ጉዳይ ይዘን ወደ ፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስልክ ብንደውልም ምላሽ ለማግኘት አልቻልንም።
በዚህ ዙሪያ የደቡብ ክልል መስተዳድርም ሆነ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ምላሽ የሚሰጡን ከሆነ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን።