(ኢሳት ዲሲ–ጥር 20/2011)በሱዳን የተጀመረው ተቃውሞ አካባቢውን ለማተራመስ የታቀደና ከቀደመው የአረብ አብዮት የተወሰደ ሃሳብ ሲሉ ጄኔራል አልበሽር ለግብጽ ፕሬዝዳንት ገለጹ።
ከወር በላይ በተቃውሞ ውስጥ የዘለቁት የሱዳን ፕሬዝዳንት ጄኔራል ዑመር አልበሽር ከግብጽ ፕሬዝዳንት ጄኔራል አብዲልፈታህ አልሲሲ ጋር ትላንት በካይሮ ባደረጉት ውይይት ይህ በሱዳን የተጀመረው አብዮት በውጭ ሃይሎች የሚደገፍ እንደሆነም መናገራቸውን አልጄዚራ ዘግቧል።
የነዳጅ ዋጋ መናርና መንግስት በዳቦ ላይ የሚያደርገው ድጎማ መቋረጡን ተከትሎ ባለፈው ወር አጋማሽ በሱዳን ተቃውሞ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሁለተኛ በሆነው የውጭ ሃገር ጉብኝታቸው ግብጽ የገቡት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኡመር አልበሽር “መጥፎ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች የአካባቢውን ሰላም ለማናጋት እየተንቀሳቀሰ ነው” በማለት ችግሩ ከሱዳን ባሻገር በአካባቢው ላይ የተነጣጠረ መሆኑን ካይሮ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክተዋል።
“ችግር እንዳለ እናውቃለን ችግሩንም እየካድን አይደለም ነገር ግን በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን እንደሚገለጸው የተጋነነ አይደለም” ያሉት የሱዳኑ ፕሬዝዳንት የአሁኑ ርምጃ የአረቡን ዓለም አብዮት በሱዳን ለመድገም የታቀደ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በታህሳስ 2011 በሙሐመድ ቡአዚዝ በተለኮሰው የአረቡ ዓለም አብዮት የቱኒዚያ፣ የግብጽ፣ የሊቢያ የየመን መሪዎች ከስልጣን መባረራቸው ሲታወስ የሶሪያው በሽር አልማድም ላለፉት 6 ዓመታት በነውጥ ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሰኔ 1989 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት የሱዳኑ አልበሽር በአረቡ ዓለም አብዮት ወቅት በሱዳን የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ በሌላ ዙር ምርጫ እንደማይሳተፉ ቃል ገብተው ከተሻገሩ በኋላ ቃላቸውን ተግባራዊ ካላደረጉ የአረብ ዓለም መሪዎች አንዱ ናቸው።
በሱዳን ዳርፉር ግዛት በተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ የተቆረጠባቸው ጄኔራል ዑመር አልበሽር የፊታችን ሰኔ ወር ስልጣን ከያዙ 30 ዓመት ይሞላቸዋል።