(ኢሳት ዲሲ–ጥር 16/2011) በአፋርና ኢሳዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆምና ዕርቅ ለማውረድ በአዲስ አበባ የሰላም ውይይት መካሄዱ ተገለጸ።
በሰላም ሚኒስቴር አማካኝነት የተካሄደው ውይይት ላይ የሁለቱም ወገኖች የሃገር ሽማግሌዎች መገኘታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ሽማግሌዎቹ በሰላም ችግሩን ለመፍታት መስማማታቸውም ተገልጿል።
የሰላም ውይይቱ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት እንዳይሆን ስጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች መንግስት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል በተፈጠረው ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።
በአፋርና በኢሳ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት በሁለቱም ወገኖች ያሉ የሃይምናኦት መሪዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ከሰላም ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ማስረጋቸው ተሰምቷል።
ከውይይቱም በኋላ በሁልቱ ወገኖች መካከል ያለውን ግጭት ለመፍታት ከስምምነት መድረሳቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
በውይይቱ ላይ የሁለቱ ወገኖች የሃይማኖት አባቶች፣የሃገር ሽማግሌዎች፣የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታና የሃገር ሽማግሌዎች መገኘታቸው ታውቋል።
በስምምነቱ መሰረትም የግጭቱን መንስኤ ለማጣራትና ግጭቱ ዳግም እንዳይከሰት ያደርጋል የተባለ የጋራ ኮሚቴ መቋቋሙም ታውቋል።
ከስምምነቱ ባሻገርም የሃይማኖት አባቶቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ወርደው ሰላም ማምጣት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሰሩም ተጠይቋል።
ጉዳዩ ይመለከታናል የሚሉ ሌሎች ወገኖች ግን ስምምነቱን በመረጃ ላይ ያልተመረኮዘና ህዝብ ምንም አይነት እምነት እንዳይኖረው ያደረገ ስምምነት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ለዚህም ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት የሰላም ስምምነት ሊያደርጉ የተቀመጡ ወገኖች በመጀመሪያ ስለግጭቱ ትክክለኛ መረጃ የሌላቸው ናቸው።
ከስምምነቱ በኋላም ለህዝብ ይፋ የሆነው መረጃ ግጭቱ የተፈጠረው በሶማሌና በአፋር ክልል አዋሳኝ መካከል አስመስሎና ስምን ቀይሮ ማቅረብ በራሱ ለጉዳዩ ምንም አይነት ትኩረት አለመሰጠቱን ያሳያል ሲሉም ይወቅሳሉ።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ሁኔታ አሁንም አረገበም ይላሉ።
በአፋርና በኢሳ ጎሳዎች መካከል ያለው ግጭት የቆየና ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ ነው።ይህ መሆኑ ደግሞ ማንኛውም አካል በግልጽ ወቶ ትክክለኛውን መግለጫ እንዳይሰጥ አድርጎታል ሲሉም ይናገራሉ ኢሳት ያነጋገራቸውና የአፋርን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ አካላት።
አሁንም በሰላም ሚኒስቴር አማካኝነት ውይይት ስለማደረጋቸው ከመገናኛ ብዙሃን ከመዘገባቸው የዘለለ መረጃ የሰጠ አካል የለም ይላሉ።
መንገዶች ተከፍተዋል የሚለው መረጃም ቢሆን ለተሽከርካሪ ክፍት መሆኑን እንጂ ያለውን እውነታ የሚያሳይ አይደለም።
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአካባቢው ተወላጆች ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ በሰላም መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑን በማሳያነት ያቀርባሉ።
ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡት አካላት እውነተኛ የሰላም ስምምነት ከሆነ መጀመሪያ የግጭቱ መንስኤ ከስር መሰረቱ መጣራት አለበት ባይ ናቸው።
ትክክለኛውን መረጃ ሳይዙ የሰላም ስምምነት ላይ ደርሰናል ማለት ህዝብን ማታለል ነው ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።