ዶክተር መረራ ጉዲና በድጋሚ ድርጅታቸው ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ

ታህሳስ 26 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦህኮ) ባለፈው ቅዳሜ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላይ ጉባኤ፤ ፓርቲውን ላለፉት 16 ዓመታት ሲመሩ የቆዩትን ዶ/ር መረራ ጉዲናን በድጋሚ የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ መረጧል ።

በ1997 ዓ.ም ከቀድሞ ቅንጅት በመቀጠል በፓርላማው ከፍተኛ ድምፅ አግኝቶ የነበረው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረትም (ኢዴኃህ)፤ እንዲፈርስ ተወስኗል።

“እርስዎ በድጋሚ የተመረጡት ፓርቲው ሌላ ሰው ስለሌለው ነው ወይ?” ተብለው  የተጠየቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና፦ ‘‘የውስጥና የውጪ ተቺዎች በእኔ ድጋሚ መመረጥ ላይ የተለያየ ኀሳብ ሊኖራቸው ይችላል። አንዳንዱ በትክክልም የእኛን እድገት በቅንነት በማየት የአመራር መለዋወጥ አስፈላጊ ነው ብሎ የሚተች አለ። ሌላው ደግሞ የድርጅቱን አቅጣጫ ለማሳት ከአባሎች በላይ ድርጅቱን እወዳለሁ ብሎ አስተያየት ሊሰጥ ይችላል። ነገር ግን የእኔ በሊቀመንበርነት መቀጠል በታማኝነት ከድርጅታችን ጋር ከቀጠሉ ሰዎች በኩል ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ አይደለም’’ ሲሉ መልሰዋል።
“እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ ገዥውን ፓርቲ ከምትተቹበት  ነጥብ አንዱ፦ ‘‘አቶ መለስ ዜናዊ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ላይ በመቆየታቸው ከመሆኑ አንፃር፤ እርሰዎ ስልጣንዎን ለሌላ ሰው በማስተላለፍ ለምን  አርአያ አይሆኑም?’’ በሚል በድጋሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፦ ‘‘የመንግስት ሥልጣንና የፓርቲ ስልጣን አንድ ዓይነት አይደለም። በመንግስት ስልጣንና በፓርቲ ስልጣን የሚሰሩ ስራዎችም የተለያዩ ናቸው። የፓርቲ ስልጣን ከግለሰቡ ሳይሆን ከፓርቲው አባላት በሚመነጭ ፍላጐትና ግፊት የሚገኝ ነው። የአንድ ፓርቲ ሊቀመንበር መሆን፤ የዋስትና ሳይሆን የአባላቱ የፍላጐት ጥያቄ ነው’’ ብለዋል-ዶክተር መረራ ጉዲና።
የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት (ኦዴኃህ) ስለፈረሰበትም ሁኔታ ተጠይቀው፤ ድርጅቱ የ1997ቱ ፓርላማ ከተጠናቀቀ በኋላ ህይወት በማጣቱና በአሁኑ ወቅት ‘‘መድረክ’’ በአዲስ መልክ በምስረታ ላይ በመሆኑ  ነው እንዲፈርስ የተወሰነው ብለዋል።
በኦህኮ ሕገ-ደንብ መሠረት የሊቀመንበሩ ስልጣን የጊዜ ገደብ እንደሌለው ያወሱት ዶ/ር መረራ፤ ቅዳሜ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ሊመረጡ የቻሉትም በዚህ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።

ምንም እንኳ እሳቸው በድጋሚ ቢመረጡም፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ አባላትና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በአዳዲስ አባላት መተካታቸውን አመልክተዋል።

ፓርቲው ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት የጠቀሱት ዶ/ር መረራ፤ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ፓርቲው በክልሉ እንደልብ እንዳይንቀሳቀስ ተፅዕኖ ስለተደረገበት  በመሆኑ ነው ብለዋል።

እንደ ሰንደቅ ዘገባ ኦህኮ ቅዳሜ ባካሄደው  በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ ከተወሰኑት  ሌሎች  ውሳኔዎች መካከል፤ ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ጋር የተጀመረውን ውህደት ማጠናከር የሚል የሚገኝበት ሲሆን፤ መድረክ ወደ ግንባር በሚያድግበት ሁኔታ ላይም  ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ኦህኮ፤ የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) በሚል ስያሜ በ1988 ዓ.ም የተመሰረተ ቢሆንም፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ተፅዕኖዎች የስም ለውጥ በማድረግ የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦህኮ) ሆኖ መቀጠሉ ይታወሳል።