ከከምባታ ጠምባሮ ወደ ከፋ ዞን በገቡ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 6/2011)ከከምባታ ጠምባሮ ወደ ከፋ ዞን ከ15ዓመታት በፊት በሰፈራ የገቡ ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ተፈጸመ።

ከመስከረም ወር ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ሲፈጸም የነበረው ጥቃት ተጠናክሮ ባለፈው ሳምንት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

ፋይል

የከምባታ ጠምባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ታከለ ነጫ ለኢሳት እንደገለጹት በጥቃቱ 37 ሰዎች ተገድለዋል። ከ30ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ለመንግስት ጥሪ ብናደርግም ቶሎ ባለመድረሱ አደጋው ሊከፋ ችሏል ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙትን በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከ15 ዓመት በፊት ነው። ምርጫ 97 አንድ ዓመት አስቀድሞ ኢህአዴግ የምርጫ ማሸነፊያ አንዱ ስትራቴጂ ያደረገው በብዙ ቁጥር የሰፈራ ፕሮግራም ማከናወን ነበር።

በዘመቻ ያለምንም ቅድመ ዝግጅት የሰፈራ ፕሮግራም ከተካሄደባቸው አካባቢዎች የከፋ ዞን ዋናው እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለይም ደረቃማ ከሆኑና በድርቅ ከሚጠቁ የከምባታ ጠምባሮ፣ ሲዳማና ወላይታ አካባቢዎች ከ10ሺ በላይ ሰዎች በሰፈራ ፕሮግራም የታቀፉ ሲሆን ወደ ካፋ ዞን ከ5ሺህ ያላነሱ ሰፋሪዎች ተጓጉዘዋል።

በወቅቱ ለኑሮ የሚመች አንድም የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ሳይከናወን የሰፈሩ 2500 የሚሆኑ ከከምባታ ጠምባሮ ዞን የመጡ ነዋሪዎች በተለያዩ ወረርሽኝ በሽታ ተጠቅተው ብዙዎች እንደሞቱ ይነገራል።

የከምባታ ጠምባሮ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር ታከለ ነጫ ለኢሳት እንደገለጹት ያንን አስቸጋሪ ቦታ ለውጠው ሃብት አፍርተው ልጆች ያሳደጉና ለወግ ማዕረግ ያበቁ የያኔው ሰፋሪዎች የዛሬዎቹ ነባር ነዋሪዎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል።

ከ2005 ዓም ወዲህ በትንኮሳ የጀመረው ጥቃት ካለፈው መስከረም ወር አንስቶ ማንነትን መነሻ ወዳደረገ ጥቃት ተለውጧል ይላሉ አስተዳዳሪው ዶክተር ታከለ።

ዶክተር ታከለ እንደሚሉት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ጥቃቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህም 37 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል። ከተገደሉት መካከል በርካታ ህጻናት ይገኙበታል።

ጥቃቱ በስለትና በጥይት መሆኑን የሚጠቅሱት ተጎጂዎች የካፋ ዞን አስተዳደር ሊደርስልን አልቻለም ሲሉ በምሬት ይገልጻሉ።

ዶክተር ታከለ የተጎጂዎቹ ሁኔታ አስደንቃጭ መሆኑን በአካል ተገኝተው ማየታቸውን ይናገራሉ።

ከ30ሺህ በላይ የሚሆኑት በትምህርት ቤቶችና በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙም ታውቋል።

ጉዳዩን በተመለከተ መንግስት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስድ ተደጋጋሚ ጥሪ መደረጉን የሚገልጹት የከምባታ ጠምባሮ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር ታከለ ነጫ ምላሽ በመዘግይቱ ጉዳቱ ሊከፋ ችሏል ብለዋል።

ከዘገየም ቢሆን መከላከያ ሰራዊት መግባቱን ነው ዶክተር ታከለ የሚገልጹት።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የከምባታ ልማት ማህበር በደቡብ አፍሪካ ከካፋ ዞን ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ ማድረጉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ማህበሩ በደቡቡ አፍሪካ ነዋሪ የሆኑ የአካባቢው ተወላጆችንንና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በመጋበዝ የገንዘብ መዋጮ አድርጓል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በተገኙበት በተካሄደው በዚሁ ስነስርዓት ኢትዮጵያውያኑ በከምባታ ተወላጆች ላይ የተፈጸመውን ግድያና መፈናቀል አውግዘዋል።