(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 18/2011)በሱዳን በዳቦና በነዳጅ ዋጋ ሳቢያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ፕሬዝንዳቱ ከስልጣን ይውረዱ የሚል ጥያቄን ይዞ መቀጠሉ ተሰማ።
የሱዳን የህክምና ባለሙያዎች ተቃውሞውን በመቀላቀል የስራ አድማ የመቱ ሲሆን የህክምና ተማሪዎችም ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል።
በዋና መዲናዋ ካርቱም በትላንትናው ዕለት በተካሄደው ተቃውሞ 9 ሰዎች መጎዳታቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በምስራቃዊው የሱዳን ግዛት በገዳሪፍ ዩኒቨርስቲ የህክምና ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩት ተማሪዎች ትናንት ረቡዕ የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ዩኒቨርስቲውን ለቀው ወተዋል።
ተማሪዎቹ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጄኔራል ኦማር አልበሽር በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን እንደለቁ ጥሪ እያቀረቡ በአድማ ላይ የሚገኙትን ሃኪሞች ተቀላቅለዋል።
የጸጥታ ሰራተኞች ሆስፒታሉን በመክበብ የሃኪሞችንም ሆነ የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ መገደባቸውም ተመልክቷል።
ለአንድ ሳምንት በቀጠለው በዚህ ግጭት ግን የሞቱት ሰዎች ቁጥር 37 መድረሱ ታውቋል።
አንድ ሳምንት ያስቆጠረው ተቃውሞ ማክሰኞ ዕለት በካርቱም የጸጥታ ሃይሎችን ለሃይል ርምጃ የጋበዘ ሲሆን 9 ሰዎች መጎዳታቸውም ታውቋል።
ላለፉት 30 ዓመታት ያህል በስልጣን ላይ የቆዩትና በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙት ጄኔራል ኦማር አልበሽር ከ7 ዓመት በፊት የአረቡ ዓለም ተቃውሞ ሲቀጣጠል ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ቃል ገብተው ነበር።
ዳግመኛ ምርጫ አልሳተፍም ያሉት ጄኔራል አልበሽር ሁኔታዎች ሲረጋጉ ቃላቸውን አጥፈዋል።