(ኢሳትዲሲ–ታህሳስ 11/2011) በኢትዮጵያ ከወሰንና ከማንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚል የተዘጋጀው ረቂቃአዋጅ ዛሬ በፓርላማ ጸደቀ።
በ33 ተቃውሞ የጸደቀው ይህ አዋጅ እንዳይጸድቅ 10 የሕወሃት የፓርላማ አባላት በፊርማ አስቀድመው ጥያቄ አቅርበዋል።
ጥያቄያቸውም አዋጁ ሕገ መንግስቱን ይጻረራል የሚል ሲሆን የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ኮሚሽኑ የማማከር እንጂ የመወሰን ስልጣን ስለሌለው ሕገ መንግስት አይጻረርም በማለት ሞግተዋል።
“የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ” በሚል ዛሬ ለፓርላማው የቀረበው አዋጅ ኮሚሽኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥናቱንና ምክረ ሃሳቡን እንደሚያቀርብ ያስረዳል።
ኮሚሽኑ ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን የክልል፣የዞንና የወረዳ የአስተዳደር ጥያቄዎችን ሳይንሳዊ በሆነ ጥናት የሚመለከታቸውን ሁሉ በማሳተፍ ሞክረ ሃሳብ እንዲያቀርብ ስልጣን ተሰጥቶታል።
ይህ ኮሚሽን የስልጣን ዘመኑ 3 አመት ሲሆን ዋናው ኮሚሽነርና ምክትሉ በፓርላማ እንደሚሰየምም ተደንግጓል።