በተለያዩ የትግራይ እስር ቤቶች የራያ ተወላጆች ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ነው ተባለ


(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 11/2011) በተለያዩ የትግራይ እስር ቤቶች ከ750 በላይ የራያ ተወላጆች ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለጸ።

የራያ የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ለኢሳትእንደገለጸው ተቃውሞ ከተነሳበት ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ በተወሰደ የጅምላ እስር 761 የራያ ተወላጆች ታስረውበአራት የትግራይ እስር ቤቶች ውስጥ ታጉረዋል።

ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ የሚገልጸው ኮሚቴው አንድ ሰው በድብደባ ምክንያት ህይወቱ ማለፉን አስታውቋል።

ከታሰሩት በተጨማሪ በርካታ የራያ ተወላጆች ደብዛቸው እንደማይታወቅም ተገልጿል።

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በትግራይ እስር ቤቶች የሚደርሰውን የራያዎች ስቃይ እንዲያስቆም ኮሚቴው ጥሪ አድርጓል።

የራያ ማንነት ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ደጀኔ አሰፋ ለኢሳት እንደገለጹት በአራት የትግራይ እስር ቤቶች 761 የራያ ተወላጆች በስቃይ ላይ ይገኛሉ።

በመቀሌ፣ በማይጨው፣ አዲሸሁና ኩይሃና እስር ቤቶች ውስጥ የታጎሩት የራያ ተወላጆች ከፍተኛ ድብደባና ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ መረጃው እንዳላቸው ነው አቶ ደጀኔ የሚገልጹት።

ከአራቱ እስር ቤቶች በተጨማሪ በትግራይ በድብቅ ቦታዎች የሚገኙ እስር ቤቶች መኖራቸውን እናውቃለን ።

በአዲስ አበባ ማዕከላዊ እንደሚፈጸሙት የስቃይ አይነቶች በእነዚህ የትግራይ ስውር እስር ቤቶችም የራያ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመባቸው ነው ብለዋል አቶ ደጀኔ።

ካለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ በአላማጣና በሌሎች የራያ አካባቢዎች እንደአዲስ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ የተሰማራው የትግራይ ልዩ ሃይል በየዕለቱ የራያ ወጣቶችንና ተጽዕኖ ይፈጥራሉ የተባሉ ግለሰቦችን እያፈነ በመውሰድ ላይ እንደሆነም አቶ ደጀኔ ይገልጻሉ።

በትግርይ በሚገኙ እስር ቤቶችና ስውር የማሰቃያ ቦታዎች የተወሰዱት የራያ ተወላጆች ባለፉት ሁለት ወራት የተፈጸሙባቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አሰቃቂ ናቸው ያሉት አቶ ደጀኔ ብልት ላይ የሃይላንድ ውሃ ከማንጠልጠል ጀምሮ ከፍተኛ ድብደባና ስቃይ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

በአሁኗ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ በተዘጋበት ዘመን የራያ ተወላጆች በትግራይ ክልል ውስጥ እየተሰቃዩ እንደሆነ የገለጹት አቶ ደጀኔ አንድ የራያ ተወላጅ በድብደባ ብዛት ህይወቱ ማለፉንም ጠቅሰዋል።

የትግራይ ክልል መስተዳድር ራያ የማንነት ጥያቄ የለውም በሚል ጥያቄውን ያነሱትን በሙሉ በእስርና ወከባ እያሰቃየ እንደሆነም ተመልክቷል።

በትግራይ እስር ቤቶች በስቃይ ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ ከ500 በላይ የራያ ተወላጆች ተፈናቅለው በራያ ቆቦ ተጠልለው እንደሚገኙም ተገልጿል።

በየእስር ቤቱ የሚገኙት የራያ ተወላጆች ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኞች የህወሃት ሰዎች በመሆናቸው በፍርድ ቤት ያለው መጉላላትና የሰብዓዊ መብት ጥሰትም ለራያ ተወላጆቹ ከፍተኛ ፈተና እንደሆነባቸው አቶ ደጀኔ ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ እየከፋ በመምጣቱ የፌደራሉ መንግስት አስቸኳይ የሆነ መፍትሄ እንዲሰጥ የራያ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ጥሪ አድርጓል።