በአማሮ ኬሌ በተከሰተ ግጭት በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ


(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ11/2011) ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦነግ አባላት ናቸው በተባሉ ታጣቂዎችና በአማሮ ኬሌ ነዋሪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት በሰውናንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስር በሚገኘውየአማሮ ወረዳና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ለሁለት ዓመት የዘለቀው ግጭት ሰሞኑን እንደ አዲስ ማገርሸቱን የአካባቢውነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

የአንድ አርሶ አደር ህይወት የጠፋበት ግጭት ከትላንት ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን ጃሎ የተሰኘ ቀበሌ በእሳት መውደሙንም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አማሮ ኬሌ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ስር የሚገኝ ወረዳ ነው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ሰላም ማጣታቸውን የሚገልጹት የወረዳው ነዋሪዎች መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ነው የሚገልጹት።

በተለይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት እንደሆኑ በሚገልጿቸው ታጣቂዎች በየጊዜው ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው ይናገራሉ።

ሰዎች ይገደላሉ።የእህል እርሻዎች ይወድማሉ። ቤቶች ይቃጠላሉ። ከብቶች ይዘረፉብናል ነው የሚሉት ከጎጂ ዞን ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች የሚገኙ የአማሮ ኬሌ ነዋሪዎች።

ባለፈው ጥቅምት ወር ውስጥ በኦነግ ታጣቂዎች ሶስት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከተገደሉ በኋላ ነገሮች እየተባባሱ መምጣታቸውንም ይገልጻሉ።

ኢሳት ያነጋገሯቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከትላንት ጀምሮ በኮሬ ዳኖ ቀበሌ የኦነግ አባላት ናቸው ባሏቸው ታጣቂዎች ጥቃት እየተፈጸመ ነው።

በዳኖ ቀበሌ የኮሬ አርሶአደሮች ንብረት የሆኑ 100 ያህል ከብቶች በኦነግ ታጣቂዎች መዘረፋቸውን ተከትሎ ግጭት ተቀስቅሷል።

በሁለቱ ወገኖች መካከል በትላንትናው ዕለት በጦር መሳሪያ ተኩስ የታገዘ ግጭት መኖሩን የሚገልጹት ነዋሪዎች የተዘረፉባቸውን ከብቶች ለማስመለስ የአማሮ ኬሌ አርሶ አደሮች ከኦነግ ታጣቂዎች ጋር መፋጠጣቸው ተመልክቷል። ስለደረሰው ጉዳት የተገለጸ ነገር የለም።

 ግጭቱ ዛሬም የቀጠለ ሲሆን አንድ የአማሮ ኬሌ አርሶ አደር በተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በዛሬው ጥቃት ጃሎ የተሰኘ ቀበሌ በእሳት መቃጠሉ ታውቋል። በዚህ ቀበሌ የሚገኙ የሙዝ፣ ሸንኮራና ቡና ማሳዎች መውደማቸውን የገለጹት ነዋሪዎች እሳቱን ማጥፋት አለመቻሉንም ጠቅሰዋል።

የአማሮ ኬሌ ነዋሪዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳሉ ይገልጻሉ።

ከአማሮ ወደ ዲላ ሀዋሳና አዲስ አበባ የሚወስዱት መንገዶች መዘጋታቸው ደግሞ ችግሩን አባብሶብናል ይላሉ።

ወደ ሀዋሳ ሄዶ ጉዳይ ለማስፈጸም 230ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚጠበቅባቸው የአማሮ ኬሌ ነዋሪዎች ባለፉት ሁለት አመታት በተፈጠረው ችግር ምክንያት ወደ ኮንሶ አርባምንጭ በማምራት 520 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ሀዋሳ እንደሚደርሱ ነው በምሬት የሚገልጹት።

የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ቢገባም ችግሩ ካለባቸው አካባቢውች ይልቅ በከተማ ውስጥ ተወስኖ በመቅረቱ መፍትሄ ሊሰጠን አልቻለም ብለዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የአማሮ ኬሌ ወረዳ አስተዳዳሪን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካልንም።