(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 10/2011)በቤንሻንጉል መንገደኞችን አሳፍሮ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ በተጠመደ የቦምብ ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ።
መንገድላይ የተቀበረው ቦምብ ፈንድቶ በርካታ ሰዎች ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።
ቦምቡን ያጠመደው አካል ማን እንደሆነ አለመታወቁን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።
የቤንሻንጉል ፖሊስ ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሐሩን እንደገለጹት ከአሶሳ ከተማ ወደ ቶንጎ ሲጓዝ በነበረ መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ የተጠመደ ቦምብ ጥቃት አድርሶ ከ10 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ጥቃቱ የተሰነዘረው በተጠመደ ቦምብ መሆኑ ቢገለጽም የአጥማጆቹ ማንነት ግን እየተጣራ ይገኛል ተብሏል።
በጥቃቱ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ነው የተገለጸው።
ቁስለኞቹ በቤጊ ሆስፒታል በመታከም ላይ መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
መለስተኛ የሕዝብ ማመላለሻው መኪና 18 ሰዎችን ጭኖ እንደነበርም ተነግሯል።
በቤንሻንጉልና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በተነሳ ግጭት በርካታ ሰዎች ሲገደሉ መቆየታቸው ይታወቃል።
በተለይም በካማሽ ዞን በተደጋጋሚ በሚፈጸም ግጭት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ከመገደላቸው ሌላ እስከ 70ሺ ሰዎች ተፈናቅለው በነቀምቴና በተለያዩ አካባቢዎች ሰፍረው እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቷል።
በሁለቱ አጎራባች ክልሎች መካከል በተነሳው ግጭት የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላት በክልሎቹ ጥያቄ ጣልቃ መግባታቸውም ይታወሳል።
ይህም ሆኖ ግን ግጭቱ አለመብረዱ አንው የሚነገረው ።
ከቤንሻንጉል ግጭት ጋር በተያያዘም ከ6 መቶ የሚበልጡ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለው ባህርዳር ከተማ እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል።
በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የኦነግና የቤሕኒን ማለትም የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የቤንሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ ሃይሎች እየተጋጩ መሆናቸው ይነገራል።