(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 5/2011) በኢትዮጵያ፣ኤርትራና ሶማሊያ መሪዎች መካከል የተጀመረው የሶስትዮሽ የምክክር መድረክ አካል የሆነ ጉብኝት ለማድረግ ትላንት ሞቃዲሾ የነበሩት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይስ አፈወርቄ ዛሬ ኬንያ ናይሮቢ ገብተዋል።
ወደስልጣን ከወጡ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶማሊያን የጎበኙት አቶ ኢሳያስ አፈወርቄ፣ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሚስተር መሃመድ አብዱላሂ ጋርበሁለቱ ሃገራትና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ተመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአልሻባብ ኮማንደር የነበረውና ከአልሻባብ የከዳው ሙክታር ሮቦው በሶማሊያ ባይድዋ መታሰሩ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ሙክታር ሮቦው የታሰረው ለሃገር ግዛት ፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር እጩ ሆኖ መቅረቡን ትከትሎ ነው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን መያዛቸውን ተከትሎ ከኤርትራ ጋር የነበረው ፍጥጫ አክትሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስመራን፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ደግሞ አዲስ አበባን እንዲሁም ጎንደር፣ሃዋሳ፣ባህርዳርንና አርባምንጭን ጎብኝተዋል።
በሁለቱ መሪዎች መካከል የተጀመረው ትብብር የሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሀመድ አብዱላሂን ጨምሮ ቀጥሏል።
ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ በቅጽል ስማቸው ፎርማጆ ወደ ኤርትራና ኢትዮጵያ በመጓዝ የሶስትዮሽ የትብብር መድረክ መፍጠራቸው ይታወቃል።
የዚህ ሒደት አካል ለተባለ ጉብኝት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሞቃዲሾ ቆይታ ካደረጉ በኋላ ወደ ጎረቤት ኬንያ አቅንተዋል።
ትብብሩ ጅቡቲን ለመጨመር በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ግንኙነት የተፈጠረ ሲሆን የኤርትራው ፕሬዝዳንት በቅርቡ ጅቡቲን እንደሚጎበኙ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቀዋል።
የፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኬንያ ጉዞ ኬንያንም ወደ ትብብሩ የማስገባት ተልዕኮ ሳይሆን እንዳልቀረም ታምኖበታል።
ትብብሩ በቀጣይ ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን ያጣምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም አፍሪካ ቀንድን የተረጋጋ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሶማሊያ በቅርቡ በሚካሄደው የአገር ግዛት ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሆኖ የቀረበው የሙክታር ሮቦው መታሰር በባይድዋ የቀሰቀሰው ተቃውሞ አለመብረዱ ታውቋል።
የቀድሞው የአሸባሪው አልሻባብ ጦር አዛዥ የነበረውና በአፍጋኒስታን የሽብር ካምፕ ስልጠና የወሰደው ሙክታር ሮቦው በቁጥጥር ስር የዋለው ትላንት ማለዳ ነው።
ሙክታር ሮቦው ከአልሻባብ ክዶ ከወጣ አንድ አመት እንዳለፈውም ታውቋል።
የሱ መክዳት አልሻባብን ለማጥቃትና ለማዳከም አግዟል የሚሉ አስተያየቶች በሶማሊያውያን ዘንድ የሚንጸባረቁ ሲሆን ግለሰቡ የአልሻባብ መስራች ከመሆኑ አንጻር አሁንም የማያምኑትና በስጋት የሚመለከቱት መኖራቸው ተመልክቷል።
በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛት በሚካሄደው የሃገር ግዛት ምርጫ ራሱን ለፕሬዝዳንትነት እጩ አድርጎ የቀረበው ሙክታር ሮቦ ታጣቂዎችንና መሳሪያ በማስገባት ላይ መሆኑ ስለተደረሰበት መታሰሩን የሶማሊያ የደህንነት ሚኒስትር ገልጸዋል።
የሙክታር ሮቦው ቃል አቀባይ እየቀረበ ያለውን ክስ አስተባብለዋል።እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በነሐሴ ወር 2017 በይፋ ሽብርን በማውገዝ ለፌደራል መንግስቱ እውቅና ሰጥቷል ብለዋል።
አሁን ግን እሱን ካሰሩ በኋላ የሶማሊያ ፌደራል መንግስት ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር በመሆን እያጠቁን ነው ሲሉ የሙክታር ሮቦው ቃል አቀባይ ከሰዋል።