(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 13/2011) ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን በፓርላማው ተመረጡ።
የወይዘሪት ብርቱካን በምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት መመረጥ ቀጣዩ ምርጫ እንዳይጭበረበርና ጨርሶውንም የማጭበርበር ዝንባሌ እንዳይኖረው ያግዛል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናግረዋል።
በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ላይ ሲቀርብ የነበረውን ክስም የሚያስቀር ርምጃ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።
ወይዘሪት ብርቱካን ለሰብሳቢነት ሲታጩ ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እንዲሁም ከሌሎች ወገኖች ጋር በተደረገው ውይይት ሁሉም በእሳቸው መመረጥ እንደተስማሙ ለፓርላማ አባላቱ ግልጽ አድርገዋል።
ላለፉት ሰባት አመታት ያህል በአሜሪካ በስደት የቆዩት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በመንግስት ጥሪ ኢትዮጵያ የገቡት ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቅምት 29/2011 ነበር።
በህግ ሙያቸው በፌደራል ፍርድ ቤት በዳኝነት እንዲሁም በለውጥ እንቅስቃሴ በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነት በኋላም በመሪነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት መሾማቸውን ከገለልተኛነት አንጻር የፓርላማ አባላት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከዜግነት ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄም አያይዘው ምላሽ ሰጥተዋል።
ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ላለፉት አመታት ከፖለቲካ ድርጅቶች ተሳትፎ ተገለው መኖራቸውን በመጥቀስ ከዜግነትም አንጻር አሁንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ አክለዋል።
ሹመታቸውን በተመለከተ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችና የሃገሪቱ አንጋፋ ዜጎች እንደተወያዩበትና ሁሉም ስምምነታቸውን እንደገለጹበት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ተናግረዋል።
ከዜግንት አንጻር የሚነሱ ጥያቄዎችን በተመለከተ የውጭ ዜጋ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን በልዩ ልዩ ሙያ መስኮች ማሳተፉ አስፈላጊ መሆኑን ግን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በአስገዳጅ ሁኔታ የውጭ ዜግነት የወሰዱ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የውጭ ፓስፖርታቸውን ቀደው ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ለመመለስ መዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።
እኛ የማንፈቅደው ጥምር ዜግነትን እንጂ የሌላ ሃገር ዜግነታቸውን ከተውና ፓስፖርታቸውን ከቀደዱ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን የሚከለክል የለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነች አንጠቀምም ብለው የሚያስቡ ዲሞክራሲ እንዳይኖር የሚፈልጉ ወገኖች የሚቀጥለው ምርጫ ዲሞክራሲያዊ እንዳይሆን ነጻ ምርጫ ቦርድ መኖሩ እንደማያስደስታቸው ገልጸዋል።
በ4 ተቃውሞና በ3 ድምጸ ተአቅቦ ዛሬ በፓርላማው ሹመታቸው የጸደቀው ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከተለያዩ ወገኖች ጋር በመነጋገር የሚመረጡ አባላትን ዝርዝር ይዘው በፓርላማ እንደሚያጸድቁም ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።
ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለህግና ስርአት ጽኑ እምነት ያላቸው፣ለዚህም ዋጋ መክፈላቸውን በተግባር ሕዝብ የመሰከረላቸው በመሆናቸው መንግስት ለቦታው እንዳጫቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናግረዋል።