በትግራይ የታሰሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የድረሱልን ጥሪ አሰሙ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 11/2011)በትግራይ በተለያዩ ድብቅ እስር ቤቶች የታሰሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መንግስትና ህዝብ እንዲደርስላቸው ጥሪ አቀረቡ።

በድብቅ በተላለፈውና የ65 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ስም ዝርዝር የሚገኝበት ወረቀት ላይ እንደመለከተው ከፌደራል መንግስቱ እውቅና ውጪ የታሰሩት እነዚህ ወታደሮች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ነው።

ፋይል

የሰሜን እዝ አባለት የሆኑት እነዚህ ወታደሮች ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ባሻ የሚደርስ ማዕረግ እንዳለቸው ለማወቅ ተችሏል።

ኩያ ይባላል። በትግራይ ከሚገኙ ስውር እስር ቤቶች አንዱ ነው።

የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሆኑ 65 ወታደሮች በእዚህ ስውር እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙና የሰበዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው መሆኑን የሚያመለክት የድረሱልን ጥሪ ቀርቧል።

በስም ዝርዝር የተገለጹት የሰራዊቱ አባላት በብሄር ማንነታቸው የተነሳ ለእስርና ለስቃይ መብቃታቸውን ነው በተሰራጨው ደብዳቤ የተመለከተው።

የመከላከያ ሚኒስቴር የቀድም የምርምርና ጥናት መምሪያ ሃላፊ ለነበሩት ለኮ/ል ደረሰ ተክሌ የትግራዩ ስውር እስር ቤት ጉዳይ አዲስ አይደለም።

በኩያ ስውር እስር ቤት ውስጥ የሚገኙት 65ቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በማዐረግ ከሻለቃ ባሻ እስከ ተራ ወታደር የሚደረሱ ናቸው።

በተለያዩ ጊዚያት ወደ ስውር እስር ቤቱ የተወሰዱት አባላቱ ጨለማ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነ ተገልጿል። በአካላቸው ላይ ከሚፈጸም ጉዳት በተጨማሪ የስነልቦና ጉዳት የሚያደርሱ ጥቃቶች እየደረሱባቸው መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኮለኔል ደረሰ ተክሌ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ በተለይ የአማራና የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ የሰራዊቱ አባል በቀላሉ የመታሰርና ጥቃት ሊፈጸምባቸው የመቻሉ ነገር የተለመደ ነው ይላሉ።

አሁንም በኩያ ስውር እስር ቤት ውስጥ በስቃይ ላይ የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊቱ አባልት በአብዛኛው የአማራና የኦሮሞ ተወላጂች ናቸው።

አራት የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የሰራዊቱ አባላትም ይገኙበታል።

ከኩያ ስውር እስር ቤት የድረሱል ጥሪ ያቀረቡት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የታሰሩበት ሁኔታ ከፌደራሉ መንግስት እውቅና ውጭ መሆኑ ተመልክቷል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላትን በትግራይ ክልል መንግስት ማሰር ከአሰራር አንጻር ግራ እንደሚያጋባ የሚገልጹ ወገኖች የህወሃትን አገዛዝ የሚተቹ የሰራዊቱ አባላት በአዛዦቻቸው አማካኝነት ለእስራትና ለተለያዩ ቅጣቶች እንደሚዳረጉ ይገልጻሉ።

በኩያ ስውር እስር ቤት የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ፌደራል መንግስት በትግራይ የሚገኙ ስውር እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው ያሉትን የሰራዊቱን አባላት መታደግ አለበት ሲሉ ጥሪም አድርገዋል።

ኮለኔል ደረሰ የአሁኑ የሰሜን እዝ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ጌታቸው ጉዲና አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ይላሉ።

በትግራይ ባዶ ስድስትን ጨምሮ በርካታ ስውር እስር ቤቶች እንደሚገኙ ይነገራል።

በተለይ የወልቃይት ተወላጆች በሺዎች ቁጥር ገብተው በህይወት ይኑሩ አይኑሮ መረጃ ያልተገኘባቸው የጉድጓድ እስር ቤቶች በተለያዩ የትግራይ አከባቢዎች እንዳሉ የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ።

ባዶ ስድስት በተሰኘው ከመሬት በታች በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በርካታ ሰዎች መገዳልቸውንና አሁንም በመቶዎች የሚቆጠሩ የወልቃይት ተወላጆች በስቃይ ላይ እንደሚገኙ ይነገራል።

በባዶ ስድስት እስር ቤት ውስጥ በስቃይ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከፍተኛ ሊቃውን እንደስራቸው አግማሴ 24 ዓመት አለፋቸው። ቤተሰብ እንዲፈቱ እየጠየቀ ነው።

የትግራይ መስተዳድር እሳቸውን ጨምሮ ደብዛቸው ስለጠፉት እስረኞች ጉዳይ ዝምታን መርጧል።

የመምህር እንድስራቸው አግማሴ ልጅ አባታቸውን ለማግኘት ቤተሰብ እየሞከረ እንደሆነ ይናገራል።

በትግራይ ስለሚገኙት ስውር እስር ቤቶችም ሆኑ በስቃይ ላይ ስለሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጉዳይ የትግራይ መስተዳድር ምላሽ እንዲሰጠን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት በሌላው የኢትዮጵያ አከባቢዎች እስር ቤቶች በራቸው ተከፍተው የግፍ ዘመናቸው እንዲያበቃ ሲያደርጉ በትግራይ አሁንም የሰው ልጅ የስቃይ ቦታ የሆኑ ስውር እስር ቤቶች ላይም ርምጃ እንዲወስዱ እየተጠየቀ ይገኛል።