(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 11/2011) በከባድ ሌብነትና በከፍተኛ የሰብአዊ መብት ረገጣ ተጠርጥረው በታሰሩና በሚፈለጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ንብረት እንዲታገድ ትዕዛዝ ወጣ።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ለ10ሩም ክፍለ ከተሞች በጻፈው ደብዳቤ የ413 ሰዎች ቤትና ንብረት ታግዶ እንዲቆም አሳስቧል።
ከ48 ሰአት በኋላ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደሚወጣም ተመልክቷል።
በአዲስ አበባ ለአስሩም ክፍለ ከተሞች ከፌደራል ፖሊስ ከተጻፈው ደብዳቤ መረዳት እንደተቻለው የቀድሞው የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊ የአቶ ጌታቸው አሰፋና ቤተሰባቸውን ጨምሮ የ413 ሰዎች ቤት፣ ንብረትና መሬት እንዲታገድ ፌደራል ፖሊስ ለአስሩም ክፍለከተሞች ደብዳቤ ጽፏል።
የብረታብረትና የኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን /ሜቴክ/ ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው እንዲሁም ወንድሞቻቸው አብርሃም ዳኘውና ኢሳያስ ዳኘው ገብረ ስላሴ ከ413ቱ ዝርዝር ውስጥ ስማቸው ተመልክቷል።
ሜጀር ጄነራል ብርሃን ነጋሽ፣ ሜጀር ጄነራል ጠና ቁርንዲ፣ ብርጋዴ ጄነራል በርሃ በየነ፣ ብርጋዴር ጄነራል ጥጋቡ ፈትለ መርሳ፣ ብርጋዴር ጄነራል ሃደጉ ገብረ ጊዮርጊስ፣ ከነቤተሰቦቻቸው ንብረታቸው እንዲታገድ ከተወሰነው ውስጥ ይገኙበታል።
ኮለኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል፣ ኮለኔል ዙፋን በርሄ፣ ኮለኔል ሸጋው ሙሉጌታ፣ ኮለኔል ጉደታ ኦላና፣ ኮለኔል ተከስተ ሃይለማርያም፣ ኮለኔል ጌትነት ጉደያ፣ ኮለኔል መሃመድ ብርሃን ከእገዳው ዝርዝር ውስጥ ከነቤተሰቦቻቸው ስማቸው ተካቷል።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ የርሳቸው ምክትል አቶ ያሬስ ዘሪሁን ከነቤተሰቦቻቸው፣ ዶክተር ሃሺም ቶፊቅ ንብረታቸው ኣንዲታገድ ከተወሰነው 413 ሰዎች ተዘርዝረዋል።
በተዘረዘሩት 413ቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ስም በግል ወይም በጋራ ወይንም በማህበር የተያዘ የመኖሩያ ቤት፣ መሬት እንዲሁም የንግድ ድርጅት ህንጻ ስለመኖሩ ተጣርቶ ታግዶ እንዲቆይ ፌደራል ፖሊስ ጠይቋል።
የፌደራል ፖሊስ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊ የነበሩትን የአቶ ጌታቸው አሰፋና የቤተሰባቸው እንዲሁም የጄነራል ክንፈ ዳኘውና ቤተሰባቸው በአጠቃላይ 205 ሰዎች የባንክ ሂሳብ እንዲታገድ ጠይቋል።