የሞያሌው ግጭት ጋብ ማለቱ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 7/2011) ለአንድ ሳምንት የዘለቀው የሞያሌው ግጭት ጋብ ማለቱ ተገለጸ።

በእስከአሁኑ ግጭት 19 ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

ፋይል

በሶማሌ ገሪና በኦሮሚያ ቦረና ተወላጆች መካከል የተፈጠረው ግጭት በአካባቢው ያለውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዳስቆመው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በግጭቱ መነሻነት ላይ ሁለቱ ክልሎች እየተወዛገቡ ናቸው።

ግጭቱ የጎሳ ሳይሆን የይዞታ ይገባኛል ጥያቄ የፈጠረው እንደሆነም እየተነገረ ነው።

የትምህርት መማሪያ ክፍሎችና የጤና ማዕከል በግጭቱ ምክንያት መቃጠላቸውም ታውቋል። ከ100 በላይ ሰዎች ከሁለቱ ወገኖች ተጎድተዋል።

ኢሳት ወደ አካባቢው ደውሎ እንዳረጋገጠው ዛሬ በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል።

ግጭቱ ዳግም ያገረሸው ባለፈው ዕሁድ ነበር። መነሻውን በተመለከተ በሁለቱ ክልሎች የሚሰጡት ምክንያቶች ተመሳሳይ ነው።

ያዝ ለቀቅ ሲያደርገው የነበረው ግጭት ለመቀስቀሱ በኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት የሚነገረው የሶማሌ ክልል ተወላጆች ይዞታቸውን ለማስፋፋት ያደረጉት ሙከራ የሚል ነው።

በሶማሌ ክልል አመራሮች የሚባለው ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ኦሮሞዎች ወሰናቸውን ተሻግረው ከሶማሌ ክልል ገብተው ሰንደቃቸውን መትከላቸው ነው።

ባለፈው ረቡዕ ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የሶማሌ ክልል ባለስልጣን ተደጋጋሚ ትንኮሳ የሚያደርገው የኦሮሚያ ሚሊሺያ እንደሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

በኦሮሚያ በኩልም የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮለኔል አበበ ገረሱ ግጭቱ መቀስቀሱን ጠቅሰው እየተነጋገርንበት ነው ብለዋል።

አንዳንድ በአካባቢው ያለውን ግጭት በተመለከተ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች የግጭቱ ዋና ማጠንጠኛ የሞያሌ ጉዳይ ነው እንደሆነ ይገልጻሉ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል የሞያሌ አካባቢ ባለስልጣን ሞያሌን ወደ ዞን ለመቀየር በሶማሌ ክልል አመራሮች በኩል ፍላጎት መኖሩና ጥያቄው መቅረቡን ይጠቅሳሉ።

የሶማሌ ክልሉ አመራር በበኩላቸው የተስፋፊነት ሙከራው በኦሮሞ ተወላጆች የተደረገና ግጭትም እንዳስነሳ ይናገራሉ።

ለቢቢሲ አስተያየት የሰጡት የሶማሌ ክልል የደህንነት አማካሪ  ከዚህ በፊት ሁለቱ ህዝቦች የይገባኛል ጥያቄ ያነሱባቸው በነበሩ አካባቢዎች የኦሮሞ ተወላጆች መጥተው ሰንደቅዓልላማቸውን መትከላቸው ሁኔታውን ወደ ግጭት ቀይሮታል ብለዋል።

በኦሮሞ ታጣቂዎች በተውሰደ እርምጃም የአንድ ትምህርት ቤት ሁለት ክፍሎች እና የጤና ኬላ መቃጠሉን አማካሪው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እስከትላንት ድርስ በቀጠለው ግጭት ከሁለቱ ወገኖች 19 ሰዎች ተገድለዋል። ከ100 በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

ኢሳት የአካባቢውን ሁኔታ ለማጣራት ዛሬ ባደረገው ሙከራ ግጭቱ መብረዱን ለማወቅ ተችሏል።

በዛሬው ዕለት በከባድ መሳሪያ ሳይቀር ሲደረግ የነበረው ግጭት ጋብ ብሎ ታይቷል። ምንም እንኳን ዘላቂ ለመሆኑ ዋስትና ባይሆንም በሁለቱ ክልሎች አመራሮች በኩል እየተካሄደ ያለው ንግግር ለጊዜው ግጭቱ እንዲበርድ እንዳደርገው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።