(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 7/2011) የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ሃላፊ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በከባድ የሌብነት ወንጀል እንደጠረጠራቸው ፖሊስ ገለፀ።
ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙት ከቀደሞው የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ዋና ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በመሆን እንደሆነም ፖሊስ ገልጿል።
እስረኞችን ለመወንጀል ሲሉ ሰዎች እያደራጁ ወደ ኤርትራ እየላኩ ህገወጥ መሳሪያ በማስገባት ሕዝብ ሲያሸብሩ መቆየታቸውም ተመልክቷል።
ተጠርጣሪው አቶ ያሬድ ዘሪሁን ካልተያዙት ግብረ አበራቸው ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በመመሳጠርና ቀጥተኛ ትዕዛዝ በመቀበል በርካታ ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት መፈፀማቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል።
አቶ ያሬድ ዘሪሁን በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦች ስውር እስር ቤት ቤት እንዲገቡ፣ ብልታቸው በፒንሳ እንዲሳብ፣ብልት ላይ ውሃ የተሞላ ላስቲክ ማንጠልጠል፣ እርቃናቸውን ጉንዳን ማስበላትና ሌሎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀም ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን መርማሪው ፖሊስ ገልጿል።
ዜጎችን በጨርቅ አፍነው በመወሰድ በሕግ ባልተፈቀደ እስር ቤት እስከ አምስት ወር መሰወር፣ራቁታቸውን ቆሻሻ ላይ በመጣል በጉንዳን እንዲበሉ ማድረግ በነዚህ ሃላፊዎች ሲፈጸሙ የነበሩ ድርጊቶች እንደሆኑም ተመልክቷል።
በድብደባ ብዛት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች መኖራቸውንም ፖሊስ ገልጿል።
ግለሰቦች ወደ ኤርትራ ሄደው ህገ ወጥ መሳሪያ እንዲያስገቡ በማቀነባበር ህዝብ እንዲሸበርና ተጠርጣሪዎች ላይ እንዲሳበብ ያደርጉ ነበር ሲልም ፖሊስ አስታውቋል።
ተጠርጣሪው አቶ ያሬድ ዘሪሁን በበኩላቸው ከህግ አማካሪያቸው ጋር መገናኘት እንደሚፈልጉ በመግለፅ ለሚቀጥለው ማክሰኞ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ከማንም ጋር እንዳልገናኝ እየተደረኩ ነው፤ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን ነው የታሰርኩት ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።
መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው ከማንም ጋር እንዳልገናኝ እየተደረኩ ነው፤ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን ነው የታሰርኩት ሲሉ ያቀረቡትን አስተባብሏል።
የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱም ተጠርጣሪው ከህግ ባለሙያ ጋር እንዲገናኙና የተጠየቀው የ14 ቀን ቀጠሮ ላይ ብይን ለመስጠት በመጭው ማክሰኞ 8 ሰዓት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ሃላፊ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን በትናትናው እለት ዱከም ከሚገኝ ሆቴል ተደብቀው መያዛቸው ይታወሳል።
እሳቸው እንዲሸሹና እንዲደበቁ ተባብረዋል የተባሉት የንስሃ አባታቸውና ሹፌራቸውም ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።