(ኢሳት ዲሲ–ህዳር 6/2011) በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ሲፈጽሙ በነበሩ ባለስልጣናት ላይ መንግስት የጀመረውን ለፍርድ የማቅረብ ዘመቻ እንደሚደግፈው ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ገለጸ።
የጥቃቱ ሰለባዎችን በተመለከተ የሰበሰባቸውን መረጃዎች ለሕግ አስከባሪ አካላት እንደሚሰጥም አስታውቋል።
የፍርድ ሔደቱ ከበቀል የጸዳ እንዲሆንም ጥሪ አቅርቧል።
ከተመሰረተ ሩብ ክፍለ ዘመን ያስቀጠረውና በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመመዝገብና በማጋለጥ የሚታወቀው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የወቅቱን የመንግስት መግለጫ በተመለከተ መግለጫ ያወጣው ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ነው።
“የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ መንግስት በመውሰድ ላይ ያለው ርምጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል በሚል ርዕስ ሰመጉ ባወጣው መግለጫ በሕግ ጥላ ስር በሚገኙ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የማሰቃየት ድርጎቶችን በተመለከተ አቃቤ ሕግ ይፋ ያደረገውን ሪፖርት ሰመጉ የሚያውቀውና ሲያጋልጠው የቆየ መሆኑንም አስታውሷል።
በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ሃሳብን የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው ሃሳባቸውን በገለጹ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ አባላት ብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠል፣የብልትን ቆዳ በፒንሳ መሳብ፣ግብረሰዶም መፈጸም፣ሴቶችን መድፈር፣እስረኞችን ከአውሬ ጋር ማሳደር ሲፈጸሙ መቆየታቸውንና ይህንንም በማጋለጥ የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ሲጎተጉት መቆየቱንም በመግለጫው አስቀምጧል።
በወህኒ ቤት ውስጥ የሚሰቃዩ ሰዎች በፍርድ ቤት የደረሰባቸውን ሰቆቃ ልብሳቸውን ጭምር አውልቀው አቤቱታ ሲያቀርቡ አድማጭ ሳያገኙ መቆየታቸውንም ዝርዝሯል።
በዚህም በፍርድ ቤቶች ላይ ህዝብ እምነት እንዳይኖረው ማድረጉንም ሰመጉ ገልጿል።
ባለፉት ሰባት ወራት የመጣውን የመንግስት አስተዳደር ለውጥ ተከትሎ በመንግስት በኩል ሲወሰዱ የነበሩ ርምጃዎች በመልካምነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው በማለት ሰመጉ በመግለጫው አስፍሯል።
ላለፉት 27 አመታት መንግስታዊ ሃላፊነትን ተገን በማድረግ በንጹሃን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ በቆዩ የብሔራዊ ደህንነት የስራ ሃላፊዎችና ድርጊቱን በቀጥታ ሲፈጽሙ በነበሩ ግለሰቦች ላይ እየተወሰደ ያለው ሕጋዊ ርምጃ የሚደገፍ ነው በማለት ገልጿል።
ሰመጉ በመግለጫው በተመሳሳይ ድርጊት ውስጥ በነበሩ ሃላፊዎችም ላይ ርምጃው እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።
ሆኖም ርምጃዎች ሁሉ ሕግን መሰረት ያደረጉና ከበቀል የጸዱ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርቧል።