(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 5/2011)በሞያሌ ግጭት ተቀሰቀሰ።
ባለፉት ሶስት ቀናት በተደረገ ግጭት 12 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ያዝ ለቀቅ ሲያደርግ የነበረው ግጭት ከእሁድ ጀምሮ ተጠናክሮ እየተካሄደ መሆኑን የሶማሌ ክልል የፕሬዝዳንቱ የህግ አማካሪ ለኢሳት ገልጸዋል።
የህግ አማካሪው አቶ ጀማል ዲሪዬ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ ስለሚችል የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች አስቸኳይ መፍትሄ ማፈላለግ አለባቸው ብለዋል።
በግጭቱ 17 ሰዎች መቁሰላቸውንም አቶ ጀማል ገልጸዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ኢሳት ያነጋገራቸው የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮለኔል አበበ ገረሱ ግጭቱ ተከስቷል።-በጎሳዎች መካከል የተፈጠረ በመሆኑ በቅርበት እየተከታተልነው ነው ብለዋል።
የሶማሌ ክልል መንግስት በክልሉ ያለው ሰላም በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል እንዳሳየ ይገልጽና የሞያሌው ግጭት ግን አደገኛ አዝማሚያ እንዳይዝ ስጋት አለኝ ሲል አስታውቋል።
ባለፉት ሶስት ቀናት በሞያሌና አካባቢዋ ያገረሸው ግጭት የ12 ሰዎችን ህይወት ማጥፋቱን የገለጹት የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የህግና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አማካሪ ናቸው።
አማካሪው አቶ ጀማል ዲሪዬ በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት የተገደሉት 12ቱ ሰዎች በአንድ ወገን ያለው መረጃ ሲሆን በሌላኛው ላይ የደረሰው ሲታከልበት ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል።
በሶማሌና በኦሮሞ ታጣቂዎች መሀል የተቀሰቀሰው ግጭት አከባቢውን ወደአዲስ የቀውስ ቀጠና የቀየረው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጀማል ዲሪዬ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጠው ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ የሚችል ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ለሰሞንኛው ግጭት መንስዔ ነው ያሉት በኦሮሚያ ታጣቂዎች የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ አቶ ጀማል ይገልጻሉ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጥበትም ጠይቀዋል። በአከባቢው የእርዳታ እህል የሚያቀርቡ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ኦሮሚያንና ሶማሌ ክልሎችን የሚያገናኙ ሁለት ዋና ዋና መንገዶች በግጭቱ ምክንያት በመዘጋታቸው እርዳታ ማቅረብ እንዳልተቻለም ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚኖረው ህዝብ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆኑን የገለጹት አቶ ጀማል የእለት ተእለት ኑሮውን ለመቀጠል እንደተቸገረ ጠቅሰዋል።
ግጭቱ ሶስት ቀናት የዘለቀ ሲሆን በሁለቱም ወገኖች በኩል እየደረሰ ያለው ጉዳትም መጨመሩን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የህግና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጀማል ዲሪዬ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ምክክር ሊያደርጉ ይገባል ይላሉ።
ባለፉት ሶስት ቀናት በሞያሌ የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኩል ያለውን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የክልሉ የጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮ/ል አበበ ገረሱ ለኢሳት ወኪል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
ኮለኔል አበበ በሞያሌ የተከሰተውን ግጭት በተለመለከተ ክትትል እየተደረገ መሆኑንና ከወትሮው የተለየ አዲስ ቀውስ እንዳልተከሰተ ገልጸው የጎሳ ግጭቱን ለማስቆም በሁለቱ ክልሎች መሀል የተጀመረውን ትብብር በማጠናከር መፍትሄ እንደሚፈለግለት አስታውቀዋል።