(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 29/2011)በኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ውስጥ የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታት በመንግስት በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
እየታዩ ያሉት ችግሮችም ከዚሁ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በማመልከትም ጦርነት የሚባል ነገር አሁን የለም ሲሉም አስረድተዋል።
ጄኔራል ብርሃኑ እንዳሉትም በቅርቡ ወደ ቤተመንግስት ተጉዘው የነበሩት ወታደሮች ቤተመንግስቱን ለመበጥበጥና ካገኙም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ለመግደል አልመው ነበር።
በሐገር መከላከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ምክትል ኤታማዦር ሹምና የዘመቻ መምሪያ ዋና ሃላፊ ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ዛሬ ለንባብ ከበቃው ከመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከወር በፊት ወደ ቤተመንስት የተንቀሳቀሱት ወታደሮች ቤተመንግስቱን የጦር ሜዳ ለማድረግ አልመው መንቀሳቀሳቸውንም ገልጸዋል።
ወታደሮቹ ወደ ቤተመንስት በተጓዙበት ወቅት አብዛኞቹ ወታደሮች ያለምንም መረጃ መጓዛቸውን አብራርተዋል።
ጥቂት ወታደሮች ግን ቤተመንግስቱን ለመበጥበጥና ካገኙም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ለመግደል አልመው መንቀሳቀሳቸውን አስታውቀዋል።
ከኦነግ ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ውስጥ አለመግባባት መፈጠሩን ገልጸዋል።
ይህም ለተከሰቱ ችግሮች አስተዋጽኦ ማድረጉን በግልጽ አስቀምጠዋል።
ኦነግ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ራሳቸው እንዲፈቱት መንግስት ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አብራርተዋል።