(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 29/2011)በአፋር ዛሬ በተካሄደ ህዝባዊ ተቃውሞ ፖሊስ የሃይል ርምጃ መውሰዱ ተገለጸ።
በአዳር ወረዳ ኤልውሃ በተሰኘች ከተማ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን የክልሉ ልዩ ሃይል በወሰደው ርምጃ በርካታ ሰዎች በስለት ተወግተውና ተደብድበው ሆስፒታል መግባታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
አንድ የሀገር ሽማግሌን ጨምሮ ሰባት ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
ኤልውሃ ከተማ ነዋሪዎች የታሰሩት በአስቸኳይ ካልተፈቱና ስለት ተጠቅመው ጉዳት ያደረሱ ፖሊሶች ለህግ ካልቀረቡ ተቃውሞውን አጠናክረው እንደሚያካሄዱ በመግለጽ ላይ ናቸው።
ለሁለት ወራት ያለማቋረጥ በህዝባዊ ተቃውሞ ላይ ያሉት አፋሮች የፌደራል መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
አፋር ዛሬም እንደመሰንበቻዋ ከህዝባዊ ተቃውሞ አልተላቀቀችም።
የህዝብ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ አይቋረጥም የሚል አቋም የደረሱ የአፋር ወጣቶች ድምጻችን ይሰማ ሲሉ ሁለት ወራቸውን አጠናቀዋል።
ዛሬም በተለያዩ የአፋር ከተሞች ህዝባዊ የተቃውሞ ትዕይንቶች ተስተናግደዋል።
በተለይም በአዳር ወረዳ ኤልውሃ በተሰኘች ከተማ የተደረገው ተቃውሞ ጉዳት የደረሰበት ሆኖ ተመዝግቧል።
የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገልጹት የዛሬው የኤልውሃው ተቃውሞ እንደሌሎቹ አካባቢዎች በሰላም አልተጠናቀቀም።
የክልሉ ልዩ ሃይል ሰላማዊ ነበር የተባለውን ተቃውሞ የሃይል እርምጃ ሲወስድበት አከባቢው ወደለየለት ሁከት መቀየሩን ነው ለማወቅ የተቻለው።
ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሁኔታ በመመልከት የአቶ ስዩም አወል አስተዳደር ስለት የያዙ ሰዎችን ሰርጎ በማስገባት የተቃውሞ ሰልፉ ታዳሚዎችን እንዲያጠቁ ሳያደርጉ አልቀረም የሚል ጥርጣሬ እንዳለቸው የአፋር አክቲቪስቶች ካሰራጩት ጸሁፍ ለመረዳት ተችሏል።
በስለት የተወጉ በርካታ ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን በፖሊስ ድብደባም ተመሳሳይ አደጋ የገጠማቸው እንደሉ ታውቋል።
በኤልውሃ ዛሬ ፖሊስ ከወሰደው የሃይል እርምጃ በተጨማሪ ሰባት ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል ተብሏል።
አንድ የሀገር ሽማግሌን ጨምሮ ሰባት የአፋር ወጣቶች በዛሬ የኤልውሃ ተቃውሞ ታፍነው ወደ እስር ቤት መወሰዳቸውን የገለጹት የአፋር አክቲቪስቶች ሁኔታው የህዝቡን ተቃውሞ ይበልጥ እያጠናከረው እንደመጣ ይናገራሉ።
የዛሬውን የፖሊስ የሃይል እርምጃ ተለትሎ ህዝቡ የታሰሩት በአስቸኳይ እንዲፈቱና ጉዳት ያደረሱ የፖሊስ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ በመጠየቅ ማስጠንቀቂያ ለክልሉ መንግስት አስተላልፏል።
የህዝብን ጥያቄ በሃይል ለመጨፍለቅ የሚደረግው ሙከራ ውጤቱ አደገኛ ነው ሲሉ ነዋሪዎች አስጠንቅቀዋል።
የፌደራል መንግስቱ ዝምታ የከፋ ዋጋ እንዳያስከትል ያሳሰበው የአፋር ህዝብ ፓርቲ ተቃውሞው ወደ አመጽ ከመቀየሩ በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግም አሳስቧል።
ዘግይቶ በደረሰን ዜናም የአፋር ክልል መሪዎች ወደ አዲስ አበባ መጠራታቸው ታውቋል።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከህውሀት አገዛዝ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት ያለው የአቶ ስዩም አወል አስተዳደር የአፋር ጉዳይ በተመለከተ ከመንግስት ሃላፊዎች ጋር እንዲወያይ ለማድረግ በፌደራሉ መንግስት አማካኝነት ጥሪ ተደርጎለታል።
ከህወህት በሚደረግላቸው ድጋፍ የአፋር ክልልና ሀብት ለህውሀት ባለሀብቶች አሳልፈው ሰጥተዋል ተብለው የሚወነጀሉት አቶ ስዩም አወል ስልጣኔ እለቃለሁ ብሉም መቼ እንደሚለቁ ግልጽ አላደረጉም።
ለውጥ ለአፋሮች ዛሬውኑ በሚል የተጀመርው ተቃውሞ በመላው የአፋር ክልል አሁንም በመካሄድ ላይ ነው።