(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 25/2011) አስተዳደራዊና የማንነት ጥያቄዎችን በሚያነሱ ዜጎች ላይ በየትኛውም መንገድ የሚወሰደው የሃይል ርምጃ ተቀባይነት የለውም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ አወጣ።
ፓርቲው ዛሬ በአዲስ አበባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአዲስ አበባ ነዋሪን የመደራጀት መብት እንዲከበር፣ የራያ የማንነት ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጠው፣ በሀረር በስርዓት አልበኞች ርምጃ ነዋሪው ላይ ለተጋረጠው አደጋ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቋል።
በንጽሃን ዜጎች ላይ የኃይል ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ የሰጡና ነፍስ ያጠፉ የጸጥታ ኃይሎች በሕግ እንዲጠየቁ ያሳሰበው ሰማያዊ ፓርቲ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ተገቢው ካሳ እንዲከፈልም በመግለጫው አመልክቷል።
የሰማያዊ ፓርቲ መግለጫ ሶስት አከባቢዎች ላይ አተኩሯል። አዲስ አአበባ፡ ራያና ሀረር።
በእነዚህ አከባቢዎች የአስተዳደርና የማንነት ጥያቄዎች በሃይል እየተመለሱ ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት እየሆኑ ነው ይላል በመግለጫው።
በየትኛውም መንገድ የሚወሰደው የሃይል እርምጃ ተቀባይነት የለውም ያለው ሰማያዊ ፓርቲ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የአስተዳዳር እና የማንነት ጥያቄዎች በምክክር እና በውይይት የሕዝብን ፍላጎት መሠረት ተደርጎ በመንግሥት በኩል አፋጣኝ ምላሽ መሰጠት ሲገባው ዜጎች መገደላቸውንና መታሰራቸውን አጥብቀን እናወግዛለን ብሏል።
አዲስ አበባን በተመለከተ አጽንኦት የሰጠው ሰማያዊ ፓርቲ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የፍትህ ትግል ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያበረከተው የአዲስ አበባ ህዝብ በቁመናው ልክ መብቱን የሚያከብርለት፣ ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥለት አመራር ያስፈልገዋል ሲል ገልጿል።
በተቃራኒው ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተለያየ መንፈስና ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የአዲስ አበባን ነዋሪ የሀገሩ ባለቤት ሳይሆን ተፈቅዶለት የሚኖር አድርገው መግለጻቸውን ያስታወሰው ሰማያዊ ፓርቲ በአዲስ አበባ ፖሊስ ነዋሪው ላይ የተወሰደው የእስር ርምጃም የማሸማቀቅ አንዱ ስልት እንደሆነ በመግለጽ በአስቸኳይ እንዲታረም ጠይቋል።
ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፌዴራል ሥርዓት በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በዜጎች መካከል ለግጭት ዋነኛ መንስሄ በመሆን ለሞት እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል ያለው ሰማያዊ ፓርቲ የፌዴራሉ አወቃቀር ባለፉት 27 ዓመታት ያመጣውን አስከፊ ችግር በተመለከተ ስጋታችንን በተደጋጋሚ ከመግለጽ ባሻገር አማራጭ ሐሳብ አቅርቤአለሁ ብሏል።
በራያ አላማጣ ሰሞኑን የተከሰተውን ውዝግብ ያነሳው ፓርቲው ዜጎች ለሚያነሱት ጥያቄ የፌዴራል መንግሥት እንዲሁም የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠታቸው የንጹሃን ዜጎች ሞት እየተበራከተ ነው ሲል አሳሳቢነቱን በመጥቀስ ኮንኗል።
የሀረርን ጉዳይ በማንሳት ጊዜው የእኛ ነን ባዮች እንዲሁም ለሕግ እና ለሥርዓት ተገዢ ያልሆኑ ግለሰቦች በፈጠሩት ችግር ሐረር ከተማ ለከፋ ችግር ተጋልጣለች በማለት ሰማያዊ ፓርቲ በመግለጫው አመልክቷል።
በመሆኑም በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ዜጎች የአስተዳደር እና የማንነት ጥያቄ በሚያነሱበት ወቅት በመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች የሚወሰደው የሃይል እርምጃ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ በመሆን ፈፅሞ እንዳይደገም ሰማያዊ ፓርቲ አሳስቧል።
በንጽሃን ዜጎች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ የሰጡና ነፍስ ያጠፉ የጸጥታ ኃይሎች በሕግ ይጠየቁ፣ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ተገቢውን ካሳ በአስቸኳይ እንዲከፈላቸው ሰማያዊ ፓርቲ ጠይቋል።