የኦጋዴ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር የሶማሌ ክልል ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መስማማቱን ሲገልጽ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣን በድርድሩ ስለ ሕዝበ ውሳኔ የተነሳ ነገር የለም በማለት የኦብነግን መግለጫ ውድቅ አደረጉ።
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 14 ቀን 2011 ዓ/ም ) ኦብነግ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገል በኢትዮጵያ መንግስትና በግንባሩ መካከል በአስመራ ሲደረግ የነበረው ድርድር በስምምነት መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበዬሁ ከሦስት ቀናት በፊት መግለጻቸው ይታወቃል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስምምነቱ በሰላም መቋጨቱን ባስታወቁበት መግለጫቸው ስለ ዝርዝር ይዘቱ ያሉት ነገር የለም። ይህን ተከትሎ የኦብነግ የውጭ ግንኙነት ፀሐፊ አቶ አህመድ ያሲን ሼክ ኢብራሂም የሶማሌ ህዝብ ዕጣ ፈንታውን በነፃነት ራሱ መወሰን እንዳለበ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት ላይ እንደደረሱ ተናግረዋል- ሲል ቢቢሲ የሶማሊኛው ፕሮግራም ዘግቧል። “በዚህም መሰረት የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን ህዝበ- ውሳኔ እንዲካሄድና ህዝቡ ከኢትዮጵያ መገንጠል ከፈለገ ያ መብት እንዲከበር፤ መቆየትም ከፈለገ ያ ውሳኔ እንዲከበርለት ውሳኔ ላይ ደርሰናል” በማለት ቃል አቀባዩ አክለው መግለጻቸውንም የዜና ቢቢሲ አመልክቷል። ህዝበ ውሳኔውንም ለማስፈፀምም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ኮሚቴ እንደሚመሰረትም ነው የተገጸው። በድርድሩ ላይ ከነበሩት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ የሆኑት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ኡመር ግን በኦብነግ ቃል አቀባይ የተገለጸው ነገር ስህተት መሆኑን ነው ምላሽ የሰጡት። “የዶክተር አብይን መንግስት ወይም የፓለቲካ አቅጣጫ ማጥላላት ወይም መቃወም መብት ቢሆንም፤ የበሬ ወለደ አይነት ተረትተረት በመፍጠር ግን መሆን የለበትም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አስመራ ላይ በተደረገው ስምምነት መሰረት ኦብነግ እንደ ሌሎች ትጥቅ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደነበሩት ተቃዋሚዎች የትጥቅ ትግሉን አቁሞ በሰላማዊ መንገድ አገር ውስጥ ገብቶ እንዲንቀሳቀስ ነው የተስማማው”ብለዋል። “በድርድሩ ስለ ህዝበ ውሳኔም ሆነ ስለ መገንጠልም የተነሳ ነገር የለም!”ሲሉም- የኦብነግ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረውታል የተባለው ገለጻ ውሸት መሆኑን ጠቁመዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፦“ ዛሬ ፦ዶክተር አብይ ሶማሌ ሊያስገነጥል ነው ብለው የሚወቅሱት፤ ትናንት ናይሮቢ ውስጥ ‘ኦሮሞ አገር እያመሰ ስለሆነ አንቀፅ 39ኝን ጥቀሱና ተገንጥለናል በሉ’ ብለው አብዲ ኢሌይን ሲያበረታቱ የነበሩት ኮንትራባንዲስቶች መሆናቸው ነው የሚገርመው”ብለዋል። አቶ ሙስጠፋ ምላሻቸውን ሲቋጩም፦”ከኮንትራባንዲስቶች ጭፍጨፋ የተረፈው የሶማሌ ህዝብ ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በሰላም ለመኖር የሚፈልግ ህዝብ ስለሆነ ፣አንዳንድ ሰዎች የፓለቲካ ቁማር መጫወቻ ባያደርጉት ጥሩ ነው” ሲሉ ምክር አስተላልፈዋል።