በአፋር ክልል የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የወጡ ዜጎች በልዩ ሃይል አባላት ጥቃት ደረሰባቸው
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 07 ቀን 2011 ዓ/ም ) የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን አንግበው በሰመራ ከተማ ወደ አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ የልዩ ሃይል አባላት በወሰዱት እርምጃ ቢያንስ 8 ሰዎች በጥይት ቆስለው ዱብቲ ሆስፒታል መግባታቸውን ነዋሪዎች በስልክ ለኢሳት ገልጸዋል። የመከላከያ ሰራዊት ገብቶ ግጭቱን ማስቆሙም ታውቋል።
የአፋር ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ሊለወጥ ባለመቻሉ በህዝቡ ላይ የሚደርሰው ችግር እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ አልሄደም። የአፋር ዱከሂና ወጣቶች ክንፍ አባል የሆነው ሙሳ ሂኮ የተንዳሆ እና የቀሰም ቀበና የስኳር ፋብሪካዎች ሲተከሉ ቃል የተገባላቸውን አገልግሎት አለማግኘታቸውን ገልጿል።
ወጣት ሙሳ ጥያቄዎቻችን ባለመመለሱ ኢትዮጵያዊነታችንን እየተጠራጠርን ነው ይላሉ። መንግስት የወጣቱን ድምጽ መስማትና ለጥያቄው አፋጣኝ መልስ መስጠት እንዳለበት በጅጅጋ የፖለቲካል ሳይንስና አለማቀፍ ግንኙነት መምህር የሆነው ሙሳ አደም ገልጿል፡፡
ወጣቶች ባቀረቡዋቸው ጥያቄዎች ዙሪያ የአፋር ክልላዊ መንግስት ምላሽ የሚሰጥ ከሆነ በሚቀጥለው ዘገባችን ይዘን እንቀርባለን።