በሳኡዲ ቆንስላ ገብቶ በዚያው የቀረው ጋዜጠኛ ጀማል ጉዳይ ዐለምን እያነጋገረ ነው። የቱርክ ሚዲያዎች ጋዜጠኛው ከሪያድ በመጡ ደህንነቶች መጠለፉን የሚጠቁም ቪዲዮ ይፋ አድርገዋል።
( ኢሳት ዜና መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ/ም ) የዛሬ አስር ቀን አካባቢ ነበር የሳኡዲ ዜግነት ያለው አንጋፋው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ በቱርክ ኢስታምቡል በሚገኘው የሳኡዲ ቖንጽላ ጽህፈት ቤት እንደገባ በዚያው የቀረው።
ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ለማስፈጸም እጮኛውን ከውጭ አቁሞ ወደ ቆንጽላ ጽህፈት ቤቱ ቅጥር ግቢ የዘለቀው ጋዜጠኛ ጀማል ፣የሳኡዲ ንጉሳውያን ቤተሰቦችን አሰራር የሚተች ጽሁፍ በተደጋጋሚ በዋሽንግተን ፖስትና በሌሎች ታላላቅ ጋዜጦች ላይ ይጽፍ ነበር።
እነሆ የሳኡዲ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት ጀማልን ከዋጠው አስረኛ ቀን በተቆጠረበት በዛሬው ዕለት የቱርክ ሚዲያዎች ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ በሳኡዲ ደህንነቶች መጠለፉን የሚጠቁም ቪዲዮ ይፋ አድርገዋል።
መገናኛ ብዙሀኑ ይፋ ያደረጉት ቪዲዮ ጀማል ቆንጽላ ጽህፈት ቤቱ የገባ ዕለት የሳኡዲ ደህንነቶች ኢስታምቡል አውሮፕላን ማረፊያ ሲገቡ እና የዚያኑ ዕለት ወደ ሪያድ ሲመለሱ የሚያሳይ ነው።
በቆንጽላው ዙሪያ የተገጠመው የደህንነት ካሜራም በዕለቱ ከግቢው ውስጥ መስተዋቱ ዙሪያውን የማያሳይ ጥቁር መኪና ሲወጣ ያመለከተ ሲሆን፣ ጋዜጠኛው ታፍኖ የወጣው በዚሁ መኪና ሳይሆን እንዳልቀረ ተገልጿል።
ጀማል ከተሰወረበት ዕለት አንስቶ እስካሁን ድረስ የቱርክ ባለሥልጣናት ጋዜጠኛው በሳኡዲ መንግስት እንደተገደለ እየገለጹ ነው። ሪያድ በበኩሏ ክሱን ማስተባበሏን ቀጥላለች።
“ሳባህ” የተባለው የቱርክ ታዋቂ ጋዜጣ ጋዜጠኛ ጀማልን አፍኖ በመውሰዱ ሴራ አስራ አምስት ያህል የሳኡዲ ደህንነቶች መሳተፋቸውን አስነብቧል።
ዓለማቀፍ ህግን በተጻረረ መልኩ የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ከቆንጽላ ጽህፈት ቤት የመታፈኑና የመሰወሩ ዜና ፤ ዓለማቀፉን ማህበረሰብ እያነጋገረ ነው።
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ሴክሬታሪ ዛሬ ለሳኡዲ አረቢያ ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራቸው ብሪታኒያ የጀማል ካሾጊን ጉዳይ አስመልክቶ ከሳኡዲ ፈጣን ምላሽ እንደምትጠብቅ አሣስበዋል።
የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ኸንት -ለሳኡዲው አቻቸው ለአደል አል ጁቢየር ባስተላለፉት በዚሁ የስልክ መልዕክት ሀገራቸው ከሳኡኢ ጋር ያላት ግንኙነት የሚቀጥለው በጋራ ሰብዓዊ እሴቶች ላይ ሲመረኮዝ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ከሳኡዲ ባለሥልጣናት ጋር እንዳልተነጋገሩ በመጠቀስ፣ ሆኖም በነገሩ ላይ ዝም እንደማይሉ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፖ ፣በጋዜጠኛ ጀማል ጉዳይ የሚደረገውን ምርመራ ለመደገፍ አሜሪካ ዝግጁ መሆኗን ለሳኡዲ አስታውቀዋል።.
የመንግስታቱ ድርጅት ኤክስፐርቶች በበኩላቸው በጀማል መሰወር ዙሪያ ዓለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፈጣን እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የሳኡዲው መሪ ልኡል መሀመድ ቢን ሰልማን ባለፈው ሳምንት በጋዜጠኛ ጀማል ላይ በሆነው ነገር እንዳዘኑና ሀገራቸው በፍለጋው ለመተባበር ዝግጁ እንደሆነች ለብሉምበርግ መናገራቸው ይታወሳል።
በሳኡዲ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት ገብቶ በዚያው ከቀረ አስረኛ ቀኑ የተቆጠረው የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ታሪክ መጨረሻ ምን ይሆን? የሚለው የብዙዎችን ትኩረት ሰቅዞ እንደያዘ ነው።