ዶ/ር አብይ አህመድና አቶ ደመቀ መኮንን ኢህአዴግን እንዲመሩ በድጋሜ ተመረጡ
( ኢሳት ዜና መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ/ም ) በሃዋሳ በመካሄድ ላይ ባለው የኢህአዴግ ጉባኤ ዶ/ር አብይ አህመድ ድምጽ ከሰጡ 177 ሰዎች ውስጥ የ176 ሰዎችን ድምጽ በማግኘት ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ 149 ድምጽ በማግኘት ምክትል ጠ/ሚኒስትር ሆነው ተመርጠዋል። የህወሃት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል 15 ድምጽ በማግኘት የምክትል ጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ አጥተዋል።
ከምርጫው በፊት የዶ/ር አብይ አህመድንና የአቶ ደመቀ መኮንን በድጋሜ ተመርጠው የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል የሚሹ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በጉባኤው ላይ የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ክርክር ተደርጎባቸዋል። አዴፓ የወልቃይት ጠገዴ እና የራያ ህዝብ የማንነት ይከበርንል ጥያቄ እንዲሁም የሱዳን ድንበር ጉዳይ እልባት እንዲያገኙ ሃሳብ አቅርቦ ሞግቷል። አሁን ያለው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮት እንዲሁም በአማራ ህዝብ ላይ የሚሰነዘረው የጥላቻ ንግግር እና የተሸዋረረ አመለካከት እንዲስተካከልም ጠይቋል።
የኦዴፓ ተወካዮችም ከሶማሊ ክልል ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ እንዲፈታ እንዲሁም ለውጡን ያልተቀበለው ክልል ለውጡን መቀበል እንደሚገባው አስተያየቶችን ሰንዝረዋል።
ኢህአዴግ ስብሰባውን ሲያጠቃልል ባወጣው መግለጫ ፣የጉባኤው ተሳታፊዎች ለውጡ እንዳይቀለበስ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጿል።
“ የፌዴራል ስርዓቱ ወሳኝ ሚና እየተጫወት ቢሆንም፣ አሁን አሁን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ሕገመንግስታዊ መብቶች ሲጣሱ እንደሚታይና ይህ እንዲቆምና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ የማንነት ጥያቄዎችም በህግ አግባብ እንዲፈቱ” አቋም ላይ መድረሳቸውንም በጉባኤው ላይ ውሳኔ ማሳለፋቸውን በአቋም መግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ስርዓት አልበኝነት እንደሚስተዋልና የህግ የበላይነት የተከበረባት አገር እንድትሆን ሁሉም የየበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም በአቋም መግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።