(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 25/2011)ዶክተር አብይ አሕመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር በመሆን በድጋሚ ተመረጡ።
ለኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበርነት ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን እንደገና ተመርጠዋል።
በዚሁም መሰረት አቶ አብይ አህመድም ሆነ አቶ ደመቀ መኮንን የጠቅላይ ሚኒስትርነቱንና የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን እንደያዙ እንደሚቀጥሉ ምርጫው አመልክቷል።
በሐዋሳ እየተካሄደ ያለው የኢሕአዴግ ጉባኤ የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጧል።
ለዚሁ የአመራርነት ስልጣን የተወዳደሩት ዶክተር አብይ አህመድ ከ177 መራጮች የ176ቱን ድምጽ በማግኘት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ ከ177 መራጮች የ149ኙን ድምጽ በማግኘት ምክትል ሊቀመንበር ተደርገዋል።
በዚሁም መሰረት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተወካዮች ከፍተኛውን የስልጣን እርከን መያዛቸው ታውቋል።
ለምክትል ሊቀመንበርነት ተወዳድረው የነበሩት የሕወሃቱ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረኪዳን 15 ድምጽ በማግኘት ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ እስካሁን በነበረው ሂደት በኢሕአዴግ ምክር ቤት ተመርጠው ግንባሩን ሲመሩ የቆዩት ዶክተር አብይ አሕመድ ናቸው።
በምክትል ሊቀመንበርነት ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን ሲመሩ ቆይተዋል።
ሁለቱም አመራሮች ሃገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት መርተዋል።
አሁንም በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በድጋሚ የግንባሩ ሊቀመናብርት ሆነው በመመረጣቸው የመንግስትንም ስልጣን ባሉበት እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።
የኢሕአዴግ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ደግሞ ኢንጂነር አወቀ ሃይለማርያም ናቸው።
እሳቸውም ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ የተገኙ መሆናቸው ነው የተነገረው።
ምክትል ሰብሳቢው ደግሞ ከደኢሕዴን የመጡት አቶ ጀማል ረዲ ናቸው።
ጸሃፊውም ከኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኦዴፓ/ የተወከሉት አቶ ብርሃኑ ፈይሳ ናቸው።
የኢሕአዴግ አመራሮች ምርጫ 12 አባላት ባሉት የምርጫ አስፈጻሚዎች የተከናወነ መሆኑንም ዘገባዎች አመልክተዋል።