(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 24/2011) ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ወደ አንድ መቶ ሺ መጠጋቱ ተገለጸ።
ነዋሪዎቹን በማፈናቀልና በማጥቃት የክልሉ ፖሊስ ሃይል መሳተፉን የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ሲገልጹ የቤንሻንጉል ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት የክልሉ ፖሊስ በድርጊቱ አልተሳተፈም ሲሉ አስተባብለዋል።
የመንግስት የአደጋ ጊዜ ሃላፊዎች በሰጡት መግለጫ እስካሁን የተፈናቀሉት ዜጎች ቁጥር 91 ሺ 348 መድረሱን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ የ16ሺ ያህል ቤተሰብ አባላት የሆኑት እነዚህን ተፈናቃዮች ለመረዳት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል።
ከነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ20ሺ የሚበልጡ ሕጻናት እናቶችና ለፍሰጡሮች መሆናቸውንም ከመንግስት ሃላፊዎች መግለጫ መረዳት ተችሏል።
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊቱ ሁኔታውን ለማረጋጋት በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የወለጋ ዞን የጸጥታ ሃላፊ አቶ ታከለ ቶሎሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በማፈናቀልና ጥቃት በማድረስ የተጠረጠሩ 10 የቤንሻንጉል ክልል ልዩ የፖሊስ ሃይል አባላት መታሰራቸውንም አቶ ታከለ ጨምረው ገልጸዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ባየታ የክልሉ ፖሊስ በወንጀሉ አልተሳተፉም ሲሉ ማስተባበያ ሰጥተዋል።