በሰሜን ሸዋ የመብራት መጥፋት በነዋሪዎቹ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው።
( ኢሳት ዜና መስከረም 24 ቀን 2011 ዓ/ም ) በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች በተከታታይ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት የኤሌትሪክ መቆራረጥ በመፈጠሩ በነዋሪዎቹ እና በባለሃብቶች ሥራ ላይ ከፍጠኛ ጫና መፍጠሩን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ። በተለይም በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በመብራት መጥፋት ምክንያት የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ተቸግረዋል። ግምቱ ከ7.2 ሚሊዮን በላይ ወጪ የወጣበት የሆስፒታል ኤክስ ሬይ ማሽንን ጨምሮ ሌሎች ማሽኖች ላይም ጉዳት ደረሶባቸዋል።
ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ የወረዳው አስተዳደር የህዝቡን ቅሬታ እልባት ለመስጠት እስካሁን የወሰደው ምንም ዓይነት እርምጃ የለም። በሰሜን ሸዋ የሚገኙ ከተሞች እየሰፉና የነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም፣ በመንግስት በኩል ላለፉት 27 ዓመታት ምንም ዓይነት አዲስ የመብራት ስቴሽኖች አልተተከሉም። ከፍተኛ አምራችና ግብር ከፋይ የሆኑትን የዞኑ ነዋሪዎች፣ የሚመጥናቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ጊዜያት ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።
ባለፈው ዓመት በዞኑ ከሁለት ሳምንት በላይ በተከታታይ መብራት መጥፋቱን ተከትሎ ወጣቶች ታላቅ የተቋዉሞ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።