(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 22/2011) ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ70ሺህ መብለጡ ተገለጸ።
የሞቱት ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ40 በላይ መድረሱ ታውቋል።
ሁለት ነፍሰጡሮች በሽሽት ላይ እያሉ መንገድ ላይ መውለዳቸውም ተመልክቷል።
የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሼ ዞን አመራሮች ከምዕራብ ኦሮሚያ አስተዳደር ጥምር ኮሚቴ ጋር የነበራቸውን ስብሰባ አጠናቀው ሲመለሱ በተሰነዘረባቸው ጥቃት አራት አመራሮች መገደላቸው ለግጭቱ መቀስቀስ ምክንያት እንደሆነም ተመልክቷል።
መስከረም 16 ቀን 2011 አራት የካማሼ ዞን ባለስልጣናት በታጣቂ ሃይሎች መገደላቸውን ተከትሎ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ማሻቀቡን የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በአብዛኛው የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች በተፈናቀሉበት በዚህ ክስተት ሁለት ነፍሰ ጡር እናቶች መንገድ ላይ መገላገላቸውም ተመልክቷል።
በአጠቃላይ የተፈናቃዮቹ ቁጥር 70ሺ መድረሱም ታውቋል።
የካማሽ ዞን ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከስብሰባ ሲመለሱ መገደላቸውን ተከትሎ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ በደረሰው የአጸፋ ጥቃት ከ40 ሰዎች መገደላቸውን የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ታከለ ቶኩማ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ለ70ሺ ሰዎች መፈናቀሉ ምክንያት በሆነውና ከ40 በላይ ሰዎች በተገደሉበት በዚህ ጥቃት ከ200 በላይ ቤቶች መቃጠላቸውም ተመልክቷል።
በሎይ ጅጋንፍ ወረዳ ዳለቻ እና ታንኮና የተባሉ ቀበሌዎች ችግሩ በዋናነት የተፈጠረባቸው እንደሆኑም ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በተፈጠረው ቀውስ የተፈናቀሉ 70ሺ ዜጎችን ለመታደግ የባንክ ሒሳብ መከፈቱን የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና በኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም የባንክ ሒሳብ መከፈቱ ይፋ ሆኗል።