በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረ ግጭት በርካቶች እንደተገደሉ እና ከስድሳ ሺህ የሚበልጡ ዜጎች እንደተፈናቀሉ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወታደሮች ትጥቃቸውን ፈተው ወደ ካምፕ እንዲገቡ መመሪያ ተላለፈ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ/ም ) በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በፈጸሙት ትንኮሳ የተቀሰቀሰ ነው የተባለውና ለሳምንት የዘለቀው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ግጭት እስካሁን ቁርጥ ያለ እልባት አላገኘም። በተለይ በካማሽ ዞን በተባባሰው በዚህ ግጭት በትንሹ ሃያ ሰዎች መገደላቸውና ከስድሳ ሺህ የሚበልጡ ሰዎች መፈናቀላቸው ይነገራል። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ፣ አንዳንዶቹ የግጭቱ ቦታዎች በጣም ርቀት ያላቸው የገጠር አካባቢ በመሆናቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች አሀዝ ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ብለዋል። የግጭቱ መንስዔ ሁለት የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለሥልጣናት በታጣቂዎች መገደላቸው ነው። መንግስት ኋላ ላይ ታጣቂዎቹ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።
እነዚህ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በካማሽ ዞን ጥቂት የማይባሉ ሰዎችን እንደገደሉና በርካታ ንብረቶችን እንዳወደሙም ተመልክቷል። ግጭቱ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ከየአቅጣጫው ግፊት እየተደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ፣ ኦነግ ጦሩን በፍጥነት ወደ ካምፕ እንዲያስገባ ጠይቀዋል። “ትላንት በወደቅንበት ቦታ ዛሬም መውደቅ አንፍልግም” ያሉት አቶ አዲሱ፣ “ከጅምር ለውጡ በተቃራኒ ከቆምን- እንደ ትላንቱ ተመልሰን መውደቅ እና መዋረድ እንደምንችል መረሳት የለበትም”ሲሉ አሣስበዋል። አቶ አዲሱ አክለውም፦“ትውልድ በከፍለው መስዋትነት ባለፉት አምስት ወራት እየታየ ባለው ለውጥ መንግስት በከፍተኛ ቁርጠኝነት ጠንካራ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። በአሸባሪነት ስም ተሰይመው የነበሩ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች እና ግለሰቦች ስያሜያቸው ተነስቶ በነጻነት በሃገራቸው እንዲንቀሳቀሱ ተደርጎዋል።የዲሞክራሲ ህግ እና ሰብአዊ መብት የሚያፍኑ ህጎች እንዲሰረዙ ወይም ተጣርተው እንዲሻሻሉ እቅጠጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው። ኦነግን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ወደ ሃገር ገብተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የዲሞክራሲ ሜዳ ለማስፋት የተወሰዱ እርምጃዎችን በትክክል ከተጠቀምንበት ከማንም በላይ ኦሮሞን የሚጠቅም ነው” ብለዋል።
ኦሮሞ በትግሉ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተንከባክቦ በመጠቀም ፖለቲካውን ወደ ትክክለኛ ዲሞክራሲ ለማሸጋገር በአንድነት ሊቆም ይገባል”ያሉት ኃላፊው፣ “ የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም -የትግል ዘዴያቸውን በፍጥነት ወደ ሰላም ትግል ማዞር አለባቸው። ከመንግስት ጋር የገቡትን ስምምነት በማክበርም የጦር ሃይላቸውን በፍጥነት ወደ ተዘጋጀው ካምፕ ማስገባት አለባቸው”ሲሉ አሣስበዋል። “የሰላም ትግል ለማድረግ ከወሰኑ ቦሃላ በሌላ በኩል በታጠቀ ኃይል በጫካ ውስጥ መንቀሳቀስ የለበትም”ያሉት አቶ አዲሱ፣ በዘመናዊ መንግስት ውስጥ የህግ የበላይነት ማስከበር እና የጦር መሳሪያዎችን መቆጣጠር የመንግስት ድርሻ ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል። “ኦሮሞ የፖለቲካ ልዩነቶችን በዘመናዊ መንገድ ማራመድ አቅቶት እንደ ትላንቱ እንዲተኩዋኮስ እንዲገዳደል እና ተመልሶ ባርነት ውስጥ እንዲወድቅ አንፍልግም”ሲሉም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።
ለዚህም በኦነግ ስም ታጥቀው በኦሮሚያ አንዳንድ አከባቢዎች የሚንቀሳቅሱትን በትእግስት እና በብስለት እየተከታተሉ መሆናቸውን የጠቂሙት ኃላፊው፣ ኦነግ የተደረሰውን ስምምነት በማክበር ታጥቆ እየተንቀሳቀሰ ያለውን ጦሩን በፍጥነት ወደተዘጋጀው ካምፕ እንዲያስገባ በድጋሚ እንጠይቃለን”ብለዋል። ከኦነግ ሃይል ውጭ ታጥቀው እየተንቀሳቀሱ ያሉትም ትጥቃቸውን ፈተው ወደ መደበኛ ስራቸው መመለስ እንዳለባቸው አቶ አዲሱ አስገንዝበዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በሰኔ አስራ ስድስቱ የአዲስ አበባ ቦምብ ፍንዳታ የተሳተፉት የኦነግ አባላት እንደሆኑ መግለጹ ይታወሳል። ፍንዳታው ኢላማ ያደረገው ዶክተር አብይን ለመግደል እንደሆነ እና የዚህ ምክንያቱም በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው ዶክተር አብይ ሀገሪቱን መምራት የለባቸውም የሚል እንደሆነ በይፋ ተገልጿል። በፍንዳታው የተሳተፉትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጠቆመው ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ፍንዳታውን በማቀነባበር ከጀርባ ሆነው ሲመሩ የነበሩትን ሰዎች በተያዘው ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።