ኢዴፓ ወደ አገራቸው ከገቡ ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚፈልግ ገለጸ
( ኢሳት ዜና መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ/ም ) በዶ/ር ጫኔ ከበደ የሚመራው ኢዴፓ መስከረም 21 ቀን 2011 ዓም ባወጣው መግለጫ ፣ “ በየትኛውም አይነት የዞረ ድምር የማወራረድ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው” በመግለጽ፣ በእንደዚህ አይነት የዜሮ ድምር ጨዋታ ውስጥ በመግባት የተጀመረውን ለውጥ ወደኋላ የሚመልሱ ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
“የስርዓት ለውጥ በኃይል ለማምጣት በትጥቅ ትግል እየታገሉ የነበሩ የተቃዋሚ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር በመደራደር ወደ አገር ቤት መግባታቸውን በተመለከተ መንግስት የስምምነት ነጥቦችን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቋል።
“አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ወደሀገራቸው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የገቡ ኃይሎች ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና ለመጫዎት ወደ አገራቸው መግባታቸውን ኢዴፓ” አድንቆ፣ በማንኛውም ለአገር፣ ለህዝብና ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ይገልጻል” ብሎአል።
ኢዴፓ “አሁን ባለን ድርጅታዊ አቅም በገዥው ፓርቲ ላይ ትርጉም ያለው ተፅእኖ ማሳደረም ሆነ የህዝብን ትግል በአግባቡ መምራት የምንችልበት አቅም ላይ አለመሆናችንን በመገንዘብ ከየትኛውም ስራዎቻችን በፊት የመተባበርና የመጠናከር ጉዳይን ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል፡፡” በማለት ተመሳሳይ እርዮተዓለምና አደረጃጀት ያላቸው ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡም ጥሪ አቅርቧል።
“የተጀመረው ተስፋ ሰጪ ለውጥ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይ የለውጡ ተዋናይ የሆኑት ወጣቶች ከስሜታዊ እንቅስቃሴዎች እራሳቸውን በማቀብ፣ የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር ለውጡን ወደፊት በሚያስኬድ ተግባራትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ እንዲያተኩሩ” ኢዴፓ ጥሪውን አቅርቧል።