በሃረር ከተማ ያለው የቆሻሻ ክምችት አስጊ ደረጃ ላይ ደረሰ።
( ኢሳት ዜና መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ/ም ) የሃረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት የደረቅ እና እርጥብ ቆሻሻን የማስወገድ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በማቋረጡ ከተማዋ በከፍተኛ የቆሻሻ ክምር እየተዋጠች ነው። ይህን ተከትሎ በከተማዋ ያጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ ይነሳል የሚል ስጋት በነዋሪዎቹ ዘንድ አሳድርዋል።
በ4ኛ፣ ሸንኮር፣ ፖሊስ ሜዳ፣ ደከር መውጫ፣ ኦጋዴን አንበሳ አካባቢዎች ከፍተኛ የቆሻሻ ክምር የተከማቸባቸው አካባቢዎች ናቸው። በተለይም ከቀላድ አንባ እና ከቀበሌ 10 ኮንዶሚኒየም ቤቶች የሚወጣው የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ ክምችት በአፋጣኝ እልባት ካልተሰጠው የከፋ የጤና ቀውስ ይፈጠራል ተብሎለታል።
የክልሉ መስተዳድር የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አፋጣኝ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጎችን ጤንነት እና ደኅንነት ለመጠበቅ አፋጣኝ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን አለመውሰዱ እንዳሳዘናቸው የከተማ ነዋሪዎችን አሳዝኗል።
በሃረር ያለው አስተዳደራዊ ችግሮች በፈጠሩት ችግር የከተማዋ ቆሻሻ እየተከማቸ መምጣቱንና የጤን እክሎች መፈጠራቸው ከዚህ በፊት ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።