(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 17/2011) ሐገር የረበሸና ሐገር የወጉ ሰዎች በሚመሰገኑበት ለሐገር የሰራ እንዴት ይወገዛል ሲሉ ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።
የሕወሃት ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የሕወሃትን 13ኛ ድርጅታዊ ጉባኤን በተመለከተ በሰጡት ቃለምልልስ ሐገር ወግቶ የተወደሰውን በስም ባይጠቅሱም ለሐገር ሰርቶ ይረገማል በሚል የጠቀሱት ኢንጂነር ስመኘው በቀለን ነው።
ኢንጂነር ስመኘውን ማን የት እንደረገመው ግን የሰጡት ማብራሪያ የለም።
የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትና የሕወሃቱ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል “ኢንጂነር ስመኘው ብሔራዊ ጀግና ነው ሊከበር ይገባል”ካሉ በኋላ “ሐገር የረበሸ፣ ሐገር የወጋ፣በሚመሰገንበት ግዜ ለሐገር የሰራ፣ለሐገር የወደቀ የሚረገምበት፣የሚወቀጥበት መሆን የለበትም የተገላቢጦሽ ነገሮች እየታዩ ናቸው”ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
መልዕክታቸው ለማን እንደሆነ በግልጽ ያላመለከቱትና ሐገር የወጋውንም በስም ያልጠቀሱት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በሕዳሴው ግድብ ላይ ተካሄደ የተባለውን ዘረፋና በሜቴክ ሳቢያ በፕሮጀክቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት አስተባብለዋል።
በ7 አመት ያልተጠናቀቀው፣ ግድቡ ላይ የማስፋፊያ ስራ በመሰራቱና አዲስ ውል በመፈጸሙ ነው ብለዋል።
“ሕዳሴው ሲጋለጥ” በሚል ርዕስ በቅርቡ በዋልታና ፋና ቴሌቪዥን በቀረበው ዛጋቢ ፊልም የሳሊኒ ፕሮጀክት ማናጀር ሪካርዶ ማሪናይና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይን ጨምሮ የተለያዩ ባለሙያዎችና ባለስልጣናት በተሳተፉበት ዘጋቢ ፊልም በሕወሃቱ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ሲመራ የነበረው ሜቴክ በእውቀትና በብቃት ማነስ ለስራው መጓተት ምክንያት መሆኑ እንዲሁም ያልሰራበት ገንዘብ ሁሉ ሲከፈለው መቆየቱ ተገልጿል።
ሜቴክ በፈጠረው ችግር ሳሊኒ ከውል ውጭ 338 ሚሊየን ዩሮ ወይንም 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ተጨማሪ እንዲከፈለው መጠየቁም ይፋ ሆኗል።