(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 16/2011) በሃገራት መካከል ያለው ትብብርና አንድነት አደጋ ላይ ወድቋል ሲሉ የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ ገለጹ።
ዋና ጸሀፊው አንቶኒዮ ጉተሬዝ በመካሄድ ላይ ባለው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደገለጹት ስርዓትና ደንብ ያስያዘውና ህዝቦች ተቀራርበው ለጋራ ዓላማ እንዲሰሩ ሲያደርግ የነበረው አንድነት እየተሸረሸረ ነው።
ይህ አንድነት በጣም በሚያስፈልገን ወቅት አደጋ ላይ መውደቁ አሳሳቢ ነው ሲሉ ዋና ጸሃፊው ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ጽንፍ የያዙ አመለካከቶች የበላይነት አግኝተው የዓለማችን ሰላምና እድገት በእጅጉ እየተፈታተኑ ነው ብለዋል አንቶኒዮ ጉተሬዝ።
በአንጻሩ ተስፋ ሰጪ ነገሮችም እንዳሉ የጠቆሙት ዋና ጸሃፊው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በመልካም ጎን ማንሳታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ትላንት በድርጅቱ የመሪዎች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የዓለም የመቻቻልና የትብብር ገመድ እየላላ ነው ብለዋል።
መተማመን እየተሰበረ ነው ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት፡ መንግስታት መሀል ያለው ትብብርና እምነት በመሸርሸሩ ዓለምን የሚገዛው በስምምነት ላይ የተመሰረተው ህግ አደጋ ላይ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ዓለማችን በመተማመን እጦት ቀውስ ውስጥ ገብታለች ያሉት አንቶኒዮ ጉተሬዝ የዕለም ህዝብ በመንግስታቸውና በተቋማት ላይ እምነት አጥተው ተስፋ እየቆረጠ ነው ሲሉ አሳሳቢነቱን በማሳየት ገልጸዋል።
የዓለም ሀገራት መሪዎች በተሰበሰቡበት ጉባዔ ላይ ዋና ጸሀፊው ዓለማችን በጽንፍ አመለካክቶች እየተሸነፈች መተባበርና መከባበር እየከሰመ ወደ አደገኛ አቅጣጫ እያመራች ነው በማለት ስጋታቸውን አስምተዋል።
በጸጥታው ምክር ቤት አባላት መሀል ያለመተማመን ችግርና መኖሩን በመጥቀስ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ብለዋል።
ለዓመታት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን፡ ዓለም ዓቀፍ ትብብሮች መደረጋቸውን፡ በመንግስታቱ ድርጅት ተቋማትን የመገንባቱ ስራ ውጤታማ መሆኑን፡ በጋራ ጥቅሞች ላይ የተመሰረተ ህግና መመሪያ መቀረጹን የዕለምን ህዝብ ከድህነት ለማውጣት መልካም ስራዎች መሰራታቸውን የጠቀሱት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እነዚህ ሁሉ ውጤታማ ተግባራት ግን ዘላቂ ስለመሆናቸው ዋስትና የለንም ሲሉ ተናግረዋል።
ዓለም በጽንፍ አመለካከቶች እየተዋጠች መምጣቷ ትብብርንና መተማምመን እያጠፋ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ጸሀፊው ይህ አካሄድ ዓለምን ወደማያባራ ግጭት ውስጥ ሊከታት እንደሚችን ብርቱ ስጋታቸው ለዓለም መሪዎች አስቀምጠዋል።
ዓለም በአሁኑ ጊዜ የምትመራበት አስተዳደር በትርምስና ብጥብጥ የተከበበ እንደሆነም በመጥቀስ ዓለም አቀፍ እሴቶች እየተደረመሱ በመጥፋት ላይ መሆናቸው የወደፊቱ ጊዜ አስጨናቂ ያደርገዋል ብለዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ዓለምን የገጠማትን ፈተና በዝርዝር ካስቀመጡ በኋላ መልካም ነገሮችም እንዳሉ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀል የተፈጠረው ሰላምን አንስተው በአወንታዊ መልኩ ገልጸውታል።
የሁለቱ ሀገራት እርቅ በአፍሪካው ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል ዋና ጸሀፊው።