(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 16/2011) የድሬዳዋ ፖሊስ ለ13 ሰዎች ሞትና ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነውን ግጭትና መንስኤ በመመርመር ውጤቱን ይፋ አደረገ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ ሐምሌ 29 /2010 ዓ.ም በተፈጠረው ግጭት በ3 መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ የ13 ንፁሀን ዜጎች ህይወት ማለፋንና በ42 ቤቶች ላይ ቃጠሎና ዝርፊያ መካሔዱን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ባደረገው ምርመራ 4 ግለሰቦች በቤት ቃጠሎ፣ 21 ግለሰቦች ደግሞ በቀጥታ በግድያው መሳተፋቸው በማስረጃ ተረጋግጧል።
በ5 ተጠርጣሪዎች ላይ ደግሞ ማስረጃ እያሰባሰበ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
ከ13 ሟቾች 8ቱ የ1 ዓመት ህፃንን ጨምሮ ከ15 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ናቸው።
በንብረት ረገድም ከ6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
በግጭቱ ወቀት ግድያ ፣የቤት ቃጠሎና የዝርፊያ ተደራራቢ ወንጀል በመፈፀሙ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ጊዜ መውሰዱን ፖሊስ አስታወቋል።
ፖሊስ ሁኔታውን መቆጣጠር በመቻሉ የታሰበው ሊሳካ አለመቻሉን የድሬዳዋ ፖሊስ ገልጿል።
ከሀምሌ 29/ 2010 ዓ.ም በኋላ ነሀሴ 29/ 2010 ዓም በድጋሚ ግጭት ለማስነሳት ተሞክሮ ነበር።
ፖሊስ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ሁኔታውን በመቆጣጠር 300 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውም ነው የተገለጸው።
ከተያዙት መካከል በ77ቱ ላይ ምርመራ አጣርቶ ለአቃቤ ህግ በመላኩ በፍርድ ቤት ክስ መመስረቱንም ፖሊስ አስታወቋል።
በድሬደዋ ሰሞኑን በቤቶች ላይ የተደረገውን ምልክት በተመለከተም ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር ተባብሮ በመስራቱ ምልክቱ ወደ ተግባር እንዳይለወጥ ተድርጓል ተብሏል።