(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 16/2011) የመስቀል ደመራ በአልን በነገው እለት በታላቅ ድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአሉ በፍቅርና በሰላም እንዲከበር ጥሪ አቅርባለች።
በአሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ከበአሉ ጋር ብተያያዘ የእስልምና እምነት ተከታዮች ነገ የሚከበረውን የመስቀል ደመራ ማስከበሪያ ቦታ በማጽዳት ለክርስቲያን ወንድምና እህት ወገኖቻቸው ያላቸውን ክብር አሳይተዋል።
ምዕመኑ የመስቀል በዓልን ሲያከበር የመስቀል መገለጫ በሆነው በፍቅርና በመተሳሰብ እንዲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መክራለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤትክርስትያን ጠቅላይ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የመስቀል በዓልን አስመልክቶ በሰጡት መግላጫ ምዕመናን የመስቀል በዓልን ሲያከብሩ የመስቀል መገለጫ በሆነው በፍቅርና መተሳሰብ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን በማጠናከር ሊሆን የገባል ብለዋል።
በዓሉ ሲከበርም ከመስቀሉ ጋር የማይገናኙና ባዕድ ከሆኑ ድርጊቶች ተቆጥቦ መሆን እንዳለበት ነው ዋና ስራ አስኪያጁ ያስገነዘቡት።
የመስቀል በዓልን ስናከብር እርስ በእርስ በፍቅር እና በመረዳዳት ከሌሎች ጋርም በመከባበር መሆን ይገባዋል ነው ያሉት።
በሀገር ውስጥም ሆን በውጭ በመላው አለም ለሚገኙ የቤተ ክርስትያኒቱ ልጆች በዓሉ በሰላም እንዲከበር እንደተለመደው በሰላምና በፍቅር እንዲተሳሰቡ መልዕክት አስተላልፍዋል።
በቅርብ ጊዜ በጅግጅጋና በቡራዩ በአዲስ አበባ አካባቢ የሞቱ ወገኖቻችን ነፍሳቸውን እንዲምር ቤተ ክርስትያን እንደምትጸልይም ተናግረዋል። ቤተክርስቲያኗ ድርጊቱን በፅኑ እንደምታወግዝም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ተናግረዋል።
ከአሁን በኋላም መሰል ችግሮች በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ እንዳይከሰቱ መንግስት የሚቻለውን ሁሉ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ቤተ ክርስትያንችን አጥብቃ ታሳስባለች ብለዋል።
መስክረም 16 የደመራ በዓል እና መስከረም 17 የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በየዓመቱ በደማቅ ስነ ስርዓት በተለያዩ አካባቢዎች እንደ የባህላቸው ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ እንደሚከበሩ በመግለጫው ተመልክቷል።