የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና አቶ ለማ መገርሳን በድጋሜ የድርጅቱ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ
( ኢሳት ዜና መስከረም 11 ቀን 2011 ዓ/ም ) የቀድሞው ኦህዴድ የአሁኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ለሶስት ቀናት በጅማ ከተማ ባካሄደው 9ኛ ድርጅታዊ ጉባዔው የቀድሞው የድርጅቱ ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን እና አቶ ለማ መገርሳን በነበሩበት እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምጽ ተመርጠዋል። አመራሮቹ እስከ ቀጣይ የድርጃታዊ ጉባኤ ድረስ በሹመታቸው ላይ ይቆያሉ።
ድርጅቱ የፓርቲው መሪዎችን ከመምረጥ በተጨማሪ የሥያሜ ለውጥ፣ ድርጅታዊ መዝሙሩን በመቀየር የቀድሞ አንጋፋ የድርጅቱን መሪዎቹንም በማሰናበት ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።
አዲሱን የኦዴፓ አመራርን አስመልክቶ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ አዳዲስ አመራሮች ወደ ፊት የመጡበት በመሆኑ ይህ ጉባኤ ከሌላው ጊዜ የተለየ ታሪካዊ ነው። በአዲስ መንፈስና ሀሳብ ለማገልገል የተነሳው ፓርቲው በፍቅርና በአንድነት ለማገልገልም ተግቶ እንደሚሰራም አስታውቀዋል። የኦሮሞ ዴሞራሲያዊ ፓርቲ ህዝቡን ለማገልገል ከዛሬ ጀምሮ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ቃል ይግባልም ብለዋል።
ዶ/ር አብይ በአማራና በኦሮሞ፣ በሲዳማና ወላይታ፣ በኦሮሞና ሶማሊ መካከል ግጭት ለመንሳቀስ የሚሞክሩ ሃይሎች፣ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ መክረዋል። የእኛ የዲሞክራሲ ለውጥ ልጅ እያሱ፣ ደርግ እና ኢህአዴግ ሞክረው እንደከሸፈባቸው አይከሽፍም ያሉት ዶ/ር አብይ፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ለውጡን እንዲያስቀጥሉ መክረዋል።