(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 11/2011) የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ዶክተር አብይ አሕመድንና አቶ ለማ መገርሳን የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ ጉባኤውን አጠናቀቀ።
9 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና 55 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ተመርጠዋል።
ነባሮቹን 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በይፋ ያሰናበተውና ሌሎችንም በተመሳሳይ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ያስወገደው የቀድሞው ኦሕዴድ የአሁኑ ኦዴፓ ከመረጣቸው 55 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት 39ኙ አዲስ መሆናቸው ተመልክቷል።
ላለፉት 28 አመታት ያህል የቆየውን ኦሕዴድ የሚለውን የፓርቲውን ስያሜ ወደ ኦዴፓ የለወጠውና አርማና መዝሙሩን ጭምር የቀየረው በዶክተር አብይ አሕመድ የሚመራው ኦዴፓ፣ አቶ ለማ መገርሳና ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ 9 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጧል።
ወይዘሮ አዳነች አበቤ፣አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ፣አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣አቶ አለሙ ሰሜ፣አቶ ፍቃዱ ተሰማና አቶ አዲሱ አረጋም የስራ አስፈጻሚው አባል ሆነዋል።
ከ55ቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ህዝብ ግንኙነት አቶ ታዬ ደንደአ ይገኙበታል።
በአዲስ ስያሜ፣አዲስ መዝሙርና አዲስ አርማ እንዲሁም አዳዲስ አመራሮችን ይዞ መንቀሳቀስ የጀመረው ኦዴፓ አቶ አባዱላ ገመዳ፣አቶ ኩማ ደምቅሳ፣አቶ ግርማ ብሩና አቶ ሽፈራው ጃርሶን ጨምሮ 14 ነባር አመራሩን ትላንት በክብር ማሰናበቱ ይታወሳል።
በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ መስከረም 16 ሕወሃት እንዲሁም አርብ መስከረም 18 ብአዴንና ደኢሕዴን ጉባኤያቸውን በመቀሌ፣ባህርዳርና ሃዋሳ እንደሚጀምሩ ታውቋል።
በመስከረም መጨረሻ ደግሞ የኢሕአዴግ ጉባኤ ይካሄዳል።