(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 10/2011) የእስራኤል መንግስት 1ሺ ቤተ እስራኤላውያንን ወደ ሃገሯ ለማስገባት መወሰኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታናሁ ገለጹ።
ወደ እስራኤል ለመግባት በኢትዮጵያ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት 8ሺ ያህል ቤተእስራኤላውያን መሆናቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
ነገር ግን የእስራኤል መንግስት የፈቀደው ለአንድ ሺ ሰዎች ብቻ መሆኑ በመብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቃውሞን አስከትሏል።
“ዘ ሪፐብሊክ”የተባለው ዲጂታል ሚዲያ እንደዘገበው የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ 1ሺ ቤተ እስራኤላውያን እንዲገቡ መወሰኑን ገልጸዋል።
ለዚህ ሲባል የተቋቋመው ልዩ ኮሚቴ በእስራኤል ልጆች ያሏቸው 1ሺ ኢትዮጵያውያን ወደ እስራኤል ኣንዲገቡ የወሰነ ሲሆን ሌሎች በመጠባበቅ ላይ ያሉ 7ሺ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ የተሰጠ ማብራሪያ የለም።
የእስራኤል መንግስት 8ሺ የሚሆኑትን ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገሩ ላለማስገባት ሲከለክል የቆየው ቤተ እስራኤላውያን አይደሉም በማለት ነው ይላሉ መረጃዎቹ።
የተፈቀደላቸው 1ሺ ሰዎችም ቢሆኑ በልጆቻቸው ምክንያት ፈቃዱን እንዳገኙ ታውቋል።
የእስራኤል መንግስት 8ሺ የሚሆኑትን ኢትዮጵያውያን የአይሁድ እምነት የሚከተሉ አይደሉም በማለት መከልከሉ ተገልጿል።
የመብት ተሟጋቾቹ ሰዎቹ ቤተእስራኤላውያን ናቸው ወደ ክርስቲያንነት የተቀየሩት በግድ ነው በሚል እየተከራከሩላቸው ይገኛሉ።
በአጠቃላይ በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን 144 ሺህ ያህል ሲሆኑ የመጀመሪያዎቹ ተጓዦች እሽራኤል የገቡት በደርግ ስርአት መጨረሻ አካባቢ እንደሆነም ታውቋል።
ላለፉት 30 አመታት ያህል በቀጠለው በዚህ ጉዞ ባለፈው አመት 1300 ቤተ እስራኤላውያን ተፈቅዶላቸው ወደ ሃገሪቱ ገብተዋል።